አትሌት አበባ አረጋዊ በኦታዋ ማራቶን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጻፈች

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በአንድ ወቅት በ1,500 ሜትር የሩጫ ውድድር ላይ በነበራት ተደጋጋሚ ስኬት የርቀቱ ልዩ ባለሙያ በመባል የምትታወቀው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አበባ አረጋዊ የ2026 የኦታዋ ማራቶንን በሴቶች ዘርፍ በአንደኝነት አጠናቃለች።

በዚሁ ውድድር ላይ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ኩፍቱ ታሂር በ2 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ኬንያዊቷ ቤቲ ቺፕኮሪር ደግሞ በ2 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በውድድሩ ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መሰረት በለጠ 4ኛ፣ መስከረም አሰፋ 5ኛ፣ መሰረት ደከቦ 7ኛ እንዲሁም ታደለች በቀለ 10ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ፈጽመዋል።

በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ የትውልድ ሀገሯን ኢትዮጵያን ወክላ በ1,500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ያገኘችውና በ2013 የሞስኮ አለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈችው አበባ አረጋዊ በ2014 የቤት ውስጥ አለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ ስዊድንን ወክላ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወሳል።

የሁለት ጊዜ የዳይመንድ ሊግ አሸናፊዋ አትሌት አበባ አረጋዊ ከዚህ የድል ጉዞዋ በኋላ በሰጠችው አስተያየት ለኦታዋ ማራቶን ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጓንና በማሸነፏም ታላቅ ደስታ እንደተሰማት ገልጻለች።

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷና ስዊድናዊቷ አትሌት አበባ አረጋዊ የኦታዋ ማራቶንን ለማሸነፍ የፈጀባት ጊዜ 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ12 ሰከንድ ነው።

የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆነው ባለቤቷ አትሌት የማነ ፀጋይም በ2014 እና በ2018 የካናዳን የቦታው ሪከርድ በመስበር ማሸነፉ ይታወሳል።

ይህ አጋጣሚ ባልና ሚስቱ የኦታዋ ማራቶንን በተለያዩ አመታት በማሸነፍ አዲስ ታሪክ በጋራ እንዲጽፉ አድርጓቸዋል።

✍️ በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ (ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል

#marathon #ottawamarathon #athletics #running #sportnews #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa

)




Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: