አብረን ከርመን አብረን ሳንሆን ቀረን!

- Advertisement -
Sidebar AD

ፋናን እንደተቀላቀልኩ አንድ ሳምንት የተሻገረኝ አይመስለኝም። በወቅቱ 7ኛ ፎቅ ላይ ከነበረው የጋዜጠኞች መሥሪያ (Workstation) እና መሰባሰቢያ ቦታ ተቀምጦ የነበረ አንድ ባለ ጆሮ-ገብ ድምፅ ከወትሮ በተለየ ስሜት ውስጥ ሆኖ ወደ ተቀመጠበት እንድጠጋው በእጁ አመለከተኝ። እዚያ ተቋም ስንገናኝ ለሁለተኛ ጊዜ ቢሆንም፣ ሰላምታውና አቀባበሉ ለከረመ ወዳጅ ይመስል ነበር።

የግራ እጁን ሁለት ጣቶች አገጩ ላይ ጭኖ፣ በቀኝ እጁ ከደረቱ ትይዩ ካስቀመጠው ወፍራም የግል ኮምፒውተር (PC) “መለስተኛ ሳጥን ብንለው😂” ውስጥ ፋይል መበርበር ጀመረ። “ይሄ ልጅ ከተዋወቅን ገና ሁለተኛ ሰላምታ ስሰጠው ነው፤ ምን ይዞብኝ ይሆን?” ብዬ ሳስብ፣ ከመቅጽበት የሆነ ፎቶ አወጣና፣ “ይሄ ልጅ አንተ ነህ አይደል?” አለኝ።

ፎቶውን ሳይ እራሴን ለመካድ ዳዳኝ። ለካስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለን፣ እነሱ ከአ/አ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርታዊ ጉዞ ወደ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በመጡ ጊዜ፣ የJOCOSA ፕሬዝዳንት ስለነበርኩ አቀባበልና ግብዣ (የውሃ😂) አድርጌላቸው ነበር። በዚያ ጊዜ ያስቀረነውን ፎቶ ነው መዞ ያሳየኝ። እኔ ግን በፍጹም አላስታወስኩትም ነበር። የተማሪነት ጊዜው አዳነ ከጋዜጠኛው አዳነ ጋር የተራራቁ ናቸው።

ከአዴ ጋር የጓደኝነት ውላችን ከዚያች ቀን የጀመረ ይመስለኛል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ደስ የሚል ቤተሰባዊ ጓደኝነት ፈጥረን ኖረናል። በእኔ ወሳኝ ደስታና ሐዘን ውስጥ እሱ አለ፤ እኔም በተመሳሳይ።

እኔ ባለቤቴን ሳጭ፣ ሽምግልና ከሄዱት ውስጥ አዴ አንዱ ነው። ሳገባም ሚዜዬ ነበር። በተቃራኒው፣ እሱ “እጮኛውን ታገቢኛለሽ?” ሲል ከተገኙት ጥቂት ወዳጆቹ መካከል እኔ ነበርኩ። ሽምግልና ከሄዱት ታላላቅ ሰዎች መካከልም ተገኝቻለሁ።ይሄን ጋብቻ በህግ ለማፅናት ቀበሌ ተገኝተው የጋብቻ ውል(80) ሲፈራረሙም አንዱ እማኝ ነበርኩ።

ይህን ሂደት በታላቅ ሥርዓት ለመቋጨትና ለሰርጉ ሲሰናዳም፣ ሚዜው ሆኜ ከአጠገቡ ለመቆም እኔ ብቻ ሳልሆን፣ ውድ ባለቤቴም የእሱ ባለቤት ሚዜ ሆና የማይረሳውን ቀን በጋራ ለማሳለፍ አቅደን፣ ልብስ ተለክተን፣ መኪና ተከራይተን ዝግጁ ብንሆንም፣ ሰርጉ ሳምንት ሲቀረው በሥራ ምክንያት ከአገር መውጣት ግዴታ ሆነብኝ።

ከዓመታት በፊት ማግባቱን ሲወስንና ሲያሳውቀኝ፣ ቀን ቆጥረን የጋብቻ እቅድ አውጥተን፣ እንደ ወንድም ቀኑን በጋራ ናፍቀን እንደከረምን ሰዎች፣ በዚህ ውብ ቀን አጠገቡ አለመቆም የሚፈጥረው ስሜት ከባድ ቢሆንም፣ መልካም ምኞትን ከማስፈር ውጪ ሌላ አማራጭ የለም።

አዴ እና B2 መልካም ጋብቻ እንዲሆንላችሁ ከውዷ ባለቤቴ ጋር እንመኝላችኋለን።
@Haikemikael_Debisa






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: