አዲስ አበባ : ኒውክለስ አጠቃላይ ሆስፒታል ተመረቀ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ከ40 በላይ በሚሆኑ የህክምና ባለሙያዎችና አጋሮች ጥምረት የተከፈተው ዘመናዊው ኒውክለስ አጠቃላይ ሆስፒታል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በዋና ከተማዋ በይፋ ተመርቋል።

ማዕከሉ አዲስ አበባን የህክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግና በከተማዋ ያለውን ከፍተኛ የህክምና አገልግሎት ፍላጎት ለማቃለል ያለመ መሆኑ በምረቃው ወቅት ተገልጿል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ፍሬሁን አየለ እንደተናገሩት፣ ተቋሙ ከ35 በላይ ስፔሻሊስት እና ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪሞችን ጨምሮ ከተለያዩ የጤና ዘርፎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የጋራ ራዕይ የተመሰረተ መሆኑን አስታውቀዋል።

የሆስፒታሉ ዋነኛ መርህ ሰብአዊ ክብርን የጠበቀና ርህራሄ የተሞላበት አገልግሎት መስጠት መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ዘመናዊ የህክምና እውቀትና ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

ዶክተር ፍሬሁን አያይዘውም ማህበረሰቡን ለማገልገል ለሚነሱ የጤና ባለሙያዎች መንግስት ከባድ መያዣ የሌለበት የብድርና የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያመቻች ጠይቀዋል።

በምረቃው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የጤና ባለሙያዎች ከተናጠል አሰራር ወጥተው በህብረት እንዲህ ያለ ግዙፍ የህክምና ማዕከል መክፈታቸው ለሌሎች አርአያ የሚሆን ተግባር ነው በማለት አድንቀዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር ከሚያከናውናቸው የኮሪደር፣ የወንዝ ዳርቻ ልማትና የህዝብ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ ጎን ለጎን፣ የግሉን የጤና ዘርፍ ለማገዝ የመሬት፣ የመሰረተ ልማት እና የካፒታል ሊዝ ፋይናንስ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ሆስፒታሉ ዜጎች ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚወስዱትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በሀገር ውስጥ ለማስቀረትና የከተማዋን የሕክምና ቱሪዝም አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ እገዛ እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው፣ ሆስፒታሉ ወደ ስራ መግባቱ ለጤናው ዘርፍ ትልቅ የምስራች መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ የጤና ፖሊሲው ከበሽታ መከላከል ባለፈ በማከም፣ በማዳንና በተሃድሶ ህክምና ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው፣ የኒውክለስ አጠቃላይ ሆስፒታል መከፈት ለዘርፉ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።

ባለሙያዎቹ የህክምና ስነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ ህዝቡን በታማኝነት እንዲያገለግሉ አደራ ያሉት ኃላፊው፣ የጤና ቢሮው ተቋሙን እንደ መንግስት ሆስፒታል በመቁጠር አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኒውክለስ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አሰፋ ሆስፒታሉ ዓለም የደረሰበትን የሕክምና መሣሪያዎችና ምቹ የሕክምና ክፍሎችን በማሟላት ከአጎራባች ሀገራት የሚመጡ ታካሚዎችን ጭምር ለማስተናገድ ሙሉ ዝግጁ ሆኗል ብለዋል።

#NucleusHospital #HealthSector #AddisAbabaHealth #MedicalTourism #EthiopiaHealthcare #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1