ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ “ኩላሊት ጤና፣ ህይወት ተስፋ” በሚል መሪ ቃል የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የገቢ ማሰባሰቢያ የሩጫ መርሀ ግብር አዘጋጀ።
እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም መነሻውን ካዛንችስ ዑራዔል በአዲሱ መንገድ ወደ ወሎ ሰፈር የሚወስደው መንገድ ላይ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ሩጫው የተጀመረ ሲሆን ከ7000 በላይ ሰዎችም ተሳትፈዋል።
በዕለቱ’ የኩላሊት ጤና ጉዳይ ያገባኛል ከሜሪጆይ ጋር እቆማለሁ’ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ልዩ ህብረ-ዝማሬዎችን እየዘመሩ ለሩጫው ትልቅ ድምቀት ሰጥተውት ነበር።
በሩጫ ወይም በአጭር የእግር ጉዞው ላይ ያገኘናቸው ተሳታፊዎች እንደነገሩን እንዲህ ዓይነት መርሀ- ግብሮች ህብረተሰቡን የማሰባሰብ አቅም ያላቸው በመሆኑ በኩላሊት ጤና ጉዳይ ላይ በቀላሉ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ወይዘሮ ጠይባ ሀሠን የስደተኞችና ተመለሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በሩጫ መርሀ ግብሩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የግንዛቤ ማስጨበጡ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
ወይዘሮ ቆንጂች ደበላ የአዲስ አበባ የሴቶችና የህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ፣የኢትዮጵያ የሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር አፎሚያ አበበ፣ የተለያዩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ፣ እና የሜሪ ጆይ የቦርድ አባላት በሩጫ መርሀ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት መገኘታቸው ታውቋል።
የመከላከያ የማርሽ ቡድን አባላት የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ከተዘመረ በኃላ ከፊት ሆነው የእግር ጉዞውን ያስጀመሩ ሲሆን ተሳታፊዎችም እነርሱን በመከተል ነበር የእግር ጉዞውን ያደረጉት።
በዚህ መርሀ ግብር ላይ የኢትዮሪልስቴት አልሚዎች ማህበር፣የዋሪት፣ የዳሸን ባንክ፣ የህብረት ባንክ ሌሎችም ተቋማት ድጋፍ በማድረግ ለመርሀ ግብሩ መሳካት የበኩላቸውን አድርገዋል።
በሩጫ መርሀ ግብሩ ላይ የታደሙት ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ፣ ከ10,000 ሰዎች በላይ ቲሸርት ገዝተው ድጋፍ ያደረጉ መሆኑን ገልፀው 7000 ሰዎች በሩጫው ላይ መሳተፋቸው ለሜሪ ጆይ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልፀዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ሌላ የግንዛቤ ማስጨበጫ የሩጫ መርሀ -ግብር በሀዋሣ ከተማ እንደሚደረግ ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ እየተደረገ ያለውን ስለ ኩላሊት የማስተማር ዘመቻ ከፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በ1986 ዓ.ም. በህግ የተቋቋመ ሀገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን ከ3 አሰርት ዓመታት በላይ በተለያዩ ክልሎች የተቀናጀ የልማት እና ሰብዓዊ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በመንግስት፤ የግሉ ዘርፍ እና በማህበረሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ የጤና አገልግሎቱን ለማጠናከር እና ማህበረሰቡን በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የሆስፒታል ግንባታ ስራዎችን በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች እያጠናከረ የሚገኝ ሲሆን በተለይም ለኩላሊት ጤና ችግሮች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የኩላሊት እጥበት ህክምና ማዕከላት በሃዋሳ፤ በአዲስ አበባ እና አርባ ምንጭ ከተሞች አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ በቅርቡ አገልግሎቱን በደብረ ብርሃን ከተማ ለመጀመር ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ይህንን አገልግሎት በሌሎች ከተሞች ለማስፋፋት እና ለማስቀጠል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
የዚህን መርሀ ግብር የሚድያ ማስተባበር ሥራ ያከናወነው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን (ዕዝራ እጅጉ ) እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።



Source: FastMereja









No comments yet.