#FastMereja I በጎፋ ዞን በላሃ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የአርሰናል (መድፈኞቹ) ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች፣ ክለባቸው ከ22 ዓመታት በኋላ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳቱን ተከትሎ የተሰማቸውን ደስታ በላሃ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለሚገኙ ሕሙማን የምግብና የለስላሳ መጠጦች ድጋፍ በማድረግ ገልጸዋል።
የክለቡ ደጋፊዎች ማኅበር ዛሬ ባከናወነው በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በገንዘብ ሲሰላ ከ25 ሺሕ ብር በላይ ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ ለሕሙማኑ ማድረሱን አስታውቋል። ደጋፊዎቹ ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል በከፍታና ዝቅታ፣ በድልና በሽንፈት ውስጥም ሆነው ከክለባቸው ጎን በጽናት መቆማቸውን ገልጸው፣ ይህ ታሪካዊ የዋንጫ ድል ማኅበረሰባዊ ኃላፊነትን በበጎ አድራጎት ለመወጣት ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው አብራርተዋል።
ይህ በሆስፒታሉ የተደረገው ድጋፍ የማኅበሩ የመጀመሪያው ቢሆንም፣ ተግባሩ በዚህ እንደማያበቃና በቀጣይም ለአቅመ ደካሞች፣ ለሕሙማንና ለሌሎች እርዳታ ለሚሹ ወገኖች የሚደረገው እገዛ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ደጋፊዎቹ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

Source: FastMereja









No comments yet.