ቦቆጂ፣ የዓለም አትሌቲክስ ማማ፤ የሻምፒዮኖች መፍለቂያ

- Advertisement -
Sidebar AD

#FastMereja I ​በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ውስጥ በቆጂን መዘንጋት የዓለምን የሩጫ ታሪክ እንደ መዘንጋት ይቆጠራል። በአርሲ ዞን፣ ሌሙ እና ቢልቢሎ ወረዳ የምትገኘው በቆጂ ከተማ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስሟ የሚታወቁትን አትሌቶች በማፍራት የኢትዮጵያን ስም ከፍ ያደረገች ታላቅ የጀግኖች ማዕከል ናት። በከተማዋ አምባሳደር በጋዜጠኛ አንዱዓለም ጌታቸው አማካኝነት የጎበኘናት ይህች ከተማ፣ ከሩጫ ሜዳ ባሻገር በባህሏ እና በልዩ አቀባበሏ ተወዳጅ መሆኗን አስመስክራለች።

​ከአዲስ አበባ ተነስተን አዳማንና አሰላን አቋርጠን ወደ በቆጂ ስንገባ፣ ከተማዋ የምትቀበለን በልዩ አየር ነው። የቆላማው ትኩሳት በአርሲው ብርድ ተተክቶ፣ ንፋሱ እንደ አትሌቶቹ አቀባበል በጋለ ስሜት ይገጥመናል። የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀዳ ሲንቄዎች እና ከንቲባዋ በባህላዊው አቀባበል “አና ዱፉ” በማለት፣ ጋቢ አልብሰው የጀመሩልን አቀባበል፤ የህዝቡን እንግዳ ተቀባይነትና የክብር መገለጫ ነው። ከንቲባ በርሃኔ ነገሰ እንደገለጹት፣ በቆጂ ለኢትዮጵያ የምታበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ በመሆኑ፣ ከተማዋን ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ስራ በልዩ ትኩረት እየተሰራበት ነው።

​የበቆጂ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የዓለምን የሩጫ ታሪክ የቀየሩ ድንቅ አትሌቶች የተፈጠሩባት፣ የአሸናፊነት መንፈስ የሚነፍስባት የተቀደሰች ምድር ናት። ደራርቱ ቱሉ፣ እጅጋየሁ ዲባባ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ታሪኩ በቀለ፣ እንዲሁም ለሜቻ ግርማ… እነዚህ ስሞች በቆጂን በዓለም የሩጫ ካርታ ላይ ያኖሩ ናቸው። ትምህርት ቤቱ ዛሬም በናፍቆት የተሞላ ነው፤ “የቀድሞ ተማሪዎቼ የት ናችሁ? እኔ ያሳደኳችሁ፣ የኮረኮምኳችሁ የትላንት ልጆቼ፣ መጥታችሁ ጎብኙኝ” እያለ በናፍቆት ይጠባበቃል። ይህ ትምህርት ቤት የዕውቀት ማዕከልነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የፈጠረው ፋይዳ ሊዘነጋ የማይችል ታሪካዊ ሃብት ነው።

​በቆጂ የሩጫ ብቻ አይደለችም! በከተማዋ እየተካሄደ ያለው የቴኳንዶ ስፖርት እንቅስቃሴ ሌላው የሚያስደንቅ ገጽታ ነው። “ዲ ቤስት ወርልድ ቴኳንዶ” የተባለ ማዕከል፣ በማስተር ደለለኝ አመራር ስር በቆጂን የቴኳንዶ ሻምፒዮኖች መፍለቂያ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት፣ የከተማዋን ስፖርታዊ ብቃት ሁለገብነት ያሳያል። ወጣቶች በሩጫ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የትግል ስፖርቶችም ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸው፣ የከተማዋን የስፖርት ስትራቴጂ ትክክለኛነት ያሳያል።


​ሌላኛው ትኩረት የሚስብ የጉብኝታችን ክፍል የቦቆጂ ሆስፒታል ነው። ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖቻችን የጤና እፎይታን እየሰጠ የሚገኘው ይህ ሆስፒታል፣ ከህክምና አገልግሎቱ ባሻገር በውስጥ ግቢው እየተከናወኑ ያሉት የማስዋብ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው። ለህጻናት እና አዋቂዎች የመዝናኛ አገልግሎት የሚሰጡ መናፈሻዎች መገንባታቸው፣ ሆስፒታሉን የከተማዋ የውበት መገለጫ እና ማህበራዊ መስተጋብር የሚፈጠርበት ስፍራ አድርጎታል።

በርካታ አትሌቶችን ያፈራችው ቦቆጂ ስቴዲየም እና የመሮጫ ትራክ የላትም፣ ከታዳጊዎች እስከ አባቶች የህዝቡ ጉጉት ቦቆጂ ስታድየም ተሰርቶ ማየት ሲሆን ይህን የህዝቡ ጉጉት ተመልክተው በተቀናጀ ስራ የቦቆጂን ስታድየም ሰርተው አጠናቀው ለመመረቅ እንደምንሄድ ተስፋ አደርጋለሁ።

​በቆጂ የታላቁ ሩጫን በስኬት እንዳስተናገደች ሁሉ፣ የከተማዋን የቱሪዝም አቅም ለመጠቀም እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ነው። በቀጣይ የቱሪስት ስፍራዎቿን፣ የተፈጥሮ ውበቷን እና ታሪካዊ መዳረሻዎቿን በጥናት በመለየት ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ እንደሚሰራ ተጠቁሟል። በቆጂ በአየርዋ፣ በታሪኳና በጀግኖቿ የምትወደድ ከተማ ናት፤ ገና ያልተነገረላት ብዙ ምስጢር ስላላት ወደፊት በድጋሜ ተመልሰን የምንጎበኛት ይሆናል።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1