እንግሊዝ ፓናማን 2-0 አሸነፈች

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በ2026 የዓለም ዋንጫ የምድብ 12 የመጨረሻ ጨዋታ እንግሊዝ ፓናማን 2-0 በማሸነፍ ምድቧን በአንደኝነት አጠናቃለች። በኒው ጀርሲ በሚገኘው ሜትላይፍ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ እንግሊዝ በመጀመሪያው አጋማሽ ተቸግራ ብትታይም፣ በሁለተኛው 45 ደቂቃ ያሳየችው ብልጫ ድልን አስገኝቶላታል።

ቤሊንግሃም የጨዋታውን አቅጣጫ ቀየረ

የእንግሊዝ አማካይ ጁድ ቤሊንግሃም የጨዋታው ዋነኛ ተጫዋች ሆኖ ተገኝቷል። በ62ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ጎል ካስቆጠረ በኋላ፣ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ለካፒቴኑ ሃሪ ኬን ሁለተኛውን ጎል ያስቆጠረ ድንቅ አሲስት አድርጓል።

የስካይ ስፖርትስ ተንታኝ ጋሪ ኔቪል ከጨዋታው በኋላ፣

“ጁድ ቤሊንግሃም ፍጹም ልዕለ ኮከብ ነው፤ የጨዋታውም ምርጥ ተጫዋች ነበር” ሲል አድናቆቱን ገልጿል።

ሃሪ ኬን ታሪክ ሰራ

ካፒቴኑ ሃሪ ኬን በጭንቅላት ያስቆጠረው ጎል በዓለም ዋንጫ 11ኛ ጎሉ ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህም ጋሪ ሊኔከርን በመብለጥ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ከፍተኛውን የጎል ቁጥር ያስመዘገበ እንግሊዛዊ ተጫዋች ሆኗል።

እንግሊዝ ያሳየችው ጥንካሬና ድክመት

እንግሊዝ በመጀመሪያው አጋማሽ የፓናማን ዝቅተኛ የመከላከል አደረጃጀት (Low Block) ለመስበር ተቸግራ ነበር። የጎል ዕድሎቿም አነስተኛ ነበሩ፣ የቡድኑም እንቅስቃሴ ከሚጠበቀው በታች መሆኑን ተንታኞች ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በቀኝ ተከላካይ ክፍል የተፈጠረው የጉዳት ችግር ለአሰልጣኝ ቶማስ ቱሄል አሳሳቢ ሆኗል። ሬስ ጄምስና ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ በጉዳት ከሜዳ ውጭ በመሆናቸው በቦታቸው የተሰለፈው ጃሬል ኳንሳ በጨዋታው ውስጥ ጉዳት አስተናግዶ ወጥቷል።

ፓናማ ተጋድላ ተሸነፈች

ፓናማ በመጀመሪያው አጋማሽ እንግሊዝን በጥሩ ሁኔታ በመቆጣጠር በፈጣን መልሶ ማጥቃት አደገኛ እድሎችን ፈጥራለች። ሆሴ ፋጃርዶ ያስቆጠረው ጎልም በኦፍሳይድ ተሰርዟል።

ሆኖም በሁለተኛው አጋማሽ የታክቲክ ትኩረቷን በማጣቷ በአምስት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ጎሎችን አስተናግዳ ከምድቡ በሽንፈት ተሰናብታለች።

የዓለም ሚዲያ ምላሽ

የዓለም ስፖርት ሚዲያዎች አሰልጣኝ ቶማስ ቱሄል በሁለተኛው አጋማሽ ያደረገውን ስልታዊ ለውጥ አድንቀዋል።

ቱሄልም ከጨዋታው በኋላ፣

“ውድድሩ እየተራመደ በሄደ ቁጥር እኛም እየጠነከርን እንሄዳለን።”

በማለት በቡድኑ ላይ ያለውን እምነት ገልጿል።

ከ82,000 በላይ ደጋፊዎች በሜትላይፍ ስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን በቀጥታ ተከታትለዋል። የስታዲየሙ ድባብም በበርካቶች “እንደ ዌምብሊ ስታዲየም” ተመሳስሎ ተገልጿል።

ወደ ጥሎ ማለፍ

እንግሊዝ ምድቧን በአንደኝነት በማጠናቀቅ ወደ 32 ቡድኖች ጥሎ ማለፍ በመግባት ጥሩ መነቃቃት ፈጥራለች። የዓለም ስፖርት ሚዲያዎችም ቡድኑ በቀጣዩ ዙር ከሴኔጋል ወይም ከዲ.አር. ኮንጎ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በተሻለ መንፈስ እንደሚገጥም ትንበያቸውን አቅርበዋል።

አለባቸው ደሳለኝ አበሻ | ለንደን 🇬🇧


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: