“ኸርት አታክ ኢትዮጵያ’ ከ200 በላይ ለሚሆኑ የልብ ሕሙማን ነጻ ሕክምና ሊሰጥ ነው!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Fastmereja I «ኸርት አታክ ኢትዮጵያ» (Heart Attack Ethiopia) የተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ 5ኛው ዙር ዘመቻው ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ውስብስብና ነጻ የልብ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን በዛሬዉ እለት በሰጡት መግለጫ አስታዉቋል።

ለዚህ በጎ ተግባር ከ55 በላይ ዓለም አቀፍ የልብ ህክምና ስፔሻሊስቶችን የያዘውና በዶክተር ተስፋዬ ተሊላ የሚመራው የህክምና ቡድን የፊታችን ቅዳሜ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ተገልጿል።

የዘንድሮው 5ኛ ዙር ዘመቻ ከተመሠረተ ጀምሮ ትልቁ ሲሆን፣ ሕክምናው በጥቁር አንበሳ፣በቅዱስ ጳውሎስ ፣ በካርዲያክ ሴንተር እና ዘንድሮ አዲስ በተጨመረው በኮሪያ ሆስፒታል በአጠቃላይ በ4 ማዕከላት ውስጥ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ይህን ህክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች ከካናዳ፣ ሕንድ፣ አሜሪካ፣ ሩዋንዳ እና ቦትስዋናን ጨምሮ ከ6 አገራት የተውጣጡ ከ55 በላይ የበጎ ፈቃደኛ የልብ ሐኪሞች፣ ሰርጅኖችና ነርሶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ህክምናዉን እንደሚሰጡ ነዉ የተገለፀዉ።

ድርጅቱ ህክምናውን በነጻ የሚሰጥ ሲሆን፣ ህሙማንን የመለየቱ ስራ እና የወረፋ ሂደት ግን በአገር ውስጥ ሆስፒታሎች አሰራር አማካኝነት በውስጥ የሚለይ መሆኑን አስረድተዋል።

የዘመቻው ዓላማ ጊዜያዊ ሕክምና መስጠት ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥ ዘላቂ አቅም መገንባት ሲሆን ለዚህም ስድስት የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ለከፍተኛ ስልጠና ወደ ሕንድ የሚላኩ ሲሆን፣ በሐምሌ 11 በሚካሄደው የጋላ ዲነር መርሐ-ግብር ላይ የሕክምና ማዕከል ግንባታ ዕቅድ (Hub-and-Spoke Plan) ይፋ እንደሚደረግ ነዉ የተገለፀዉ።

ድርጅቱ ለጤና ሚኒስቴር፣ የሕክምና ቁሳቁሶችን በነጻ ላጓጓዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድና ለባለሙያዎች ምስጋና ያቀረበ ሲሆን፣ ይህንን ሰብአዊ ሥራ ለማገዝ እያንዳንዱ አካል ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

በዶክተር ኦብስኔት መርዕድ እና በዶክተር ተስፋዬ ተሊላ የተመሠረተው ተቋም ላለፉት ሁለት ዓመታት ከስድስት ወራት በላይ በነጻ ሕክምና ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣ ባለፉት አራት ዙሮች ብቻ ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ወጪ በመሸፈን የ461 ሰዎችን ሕይወት መታደግ ችሏል።

#ጤና






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1