«የማይናገረው ልዑል» መጽሐፍ በታላቅ ድምቀት ሊመረቅ ነው

- Advertisement -
Sidebar AD

• በእናት የተጻፈ በአይነቱ የመጀመሪያው እውነተኛ የህይወት ታሪክ ነው

#Ethiopia | አዲስ አበባ — ደራሲ መሠረት ክንፈ ኃይሌ ከኦቲዝም ጋር ከሚኖረው ልጇ ልዑል ጋር ያሳለፈችውን ውጣ ውረድ፣ ጽናት፣ ተስፋ፣ እምነት፣ የእናትነት ፍቅርና ለልጅ የተከፈለ መስዋዕትነት ያጋራችበት «የማይናገረው ልዑል » የተሰኘው አዲስ መጽሐፍ በመጪው ቅዳሜ ሰኔ 27 ቀን 2018 ዓ.ም. በኃይሌ ግራንድ ሆቴል ይመረቃል።

መጽሃፉ በኦቲዝም ዙሪያ በአንድ ወላጅ እናት ተጽፎ ለንባብ የበቃ በሀገራችን የመጀመሪያው መጽሐፍ ነው።

ይህን ልብ ሰቃይ እውነተኛ የህይወት ታሪክ በከፍተኛ ጥራት ለአንባብያን እንዲመች አድርጎ የአርትኦትና ቅንብር ስራውን የሰራው ታዋቂው ጋዜጠኛና አርታኢ መላኩ ብርሃኑ ነው። ጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑ ከመደበኛ የኮሚዩኒኬሽን ስራው ባሻገር በበጎ ፍቃድ በኦቲዝም ላይ ግንዛቤ በመፍጠር እና ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ ልጆችና ወላጆቻቸው መብቶች በመታገል የሚታወቅ የኦቲዝም አድቮኬት ነው።ከዚህ ቀደምም ከህጻናት ክህምናና ኦቲዝም ስፔሻሊስት ዶክተር ሃዲያ ይማም ጋር “የኦቲዝም ምስጢሮች” በሚል ርዕስ የተሰናዳ መጽሃፍ በትብብር አዘጋጅቶ ለንባብ ያበቃ ባለሙያም ነው።

“የማይናገረው ልዑል” መጽሃፍ ባለታሪኳና ደራሲዋ መሰረት ክንፈ ሃይሌ ልጇ ልዑል ኦቲዝም እንዳለበት ካወቀችበት ጊዜ ጀምሮ በሃገረ አሜሪካ የልጇን የመማርና በእንክብካቤ የመያዝ መብት ለማስከበር ያደረገችውን እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ፣ እንዲሁም እንደእናት ልጇን ለመርዳት የከፈለችውን መስዋዕትነትና የገጠሟትን ተስፋ አስቆራጭ የህይወት ምስቅልቅሎች የተወጣችበትን ጥንካሬ በልብ አንጠልጣይ ትረካ ያካፈለችበት መጽሃፍ ነው።

ባለፈው ጁን 6 ቀን 20206 በአሜሪካ ሲያትል ከተማ በታላቅ ድምቀት የተመረቀው ይህ መጽሃፍ ብዙዎች እንደመሰከሩት በመላው አለም ላሉና ከኦቲዝም ጋር የሚኖር ልጅ ለሚያሳድጉ ሚሊዮኖች እናቶች የሚያሳልፉትን ውጣውረድ የሞላበት ህይወት የሚያሳይ መስተዋት ነው።

የህ “የማይናገረው ልዑል” መጽሐፍ፤ በቅርቡ በቀረቡ የሚዲያ ዘገባዎች የተነሳ በህብረተሰቡ ውስጥ በኦቲዝምና በወላጅነት ዙሪያ ትልቅ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል።

በመጪው ቅዳሜ በሚካሄደው በዚህ ልዩ የመጽሃፍ ምረቃ መድረክ ላይ በርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ ታዋቂ የልዩ ፍላጎት ምሁራን፣ ወላጆች፣ በኢትዮጵያ በኦቲዝም ላይ የሚሰሩ ተቋማት መሪዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የጥበብ ሰዎችና ሚዲያዎች እንደሚታደሙበትም ታውቋል ።

በዕለቱ በልዩ ፍላጎትና በኦቲዝም ምልከታዎች፣ በወላጅነት ስነልቡና፣ በመጽሃፉ ፋይዳ፣ በአመለካከት ለውጥ እና ኦቲዝምን በመቀበል በኩል ያሉ ክፍተቶችን ጨምሮ የመጽሐፉን ልብ ሰቃይ አንቀጾችና ዲስኩሮች የማንበብ ስነ-ስርዓት እንዲሁም ጥልቅ የመጽሐፍ ምልከታ (Review) የሚቀርብበት ልዩ መርሃ-ግብር ተዘጋጅቷል።

የዕለቱ የመድረኩ ንጉስ ታዬ ወርቁ መርሃ ግብሩን በሙያዊ ብቃቱ ያሰናስለዋል።

ይህንን መርሃግብር ለመታደም ፍላጎቱ ላለው ማንኛውም ሰው መድረኩ ነጻና ክፍት መሆኑንም ደራሲዋና አርታኢው ተናግረዋል።

ለንባብ በሚጋብዝ ውበት የመጽሃፉን የውስጥ ገጽ አቀማመጥና አጠቃላይ የዲዛይን ስራውን ወጣት ዲዛይነር አክሊሉ ድልነሳ በጥበባዊ ብቃት ሰርቶታል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን) ሚዲያና ኮሙኒኬሽንስ፣ ድሬ ቲዩብ፣ አርትስ ቲቪ፣ ፋና ቴሌቪዠን፣ አራዳ ኤፍኤም እና በርካታ ሚዲያዎች የመርሃግብሩ የሚዲያ አጋሮች ሲሆኑ የኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ማዕከል በዚህ መጽሃፍ ምረቃ መርሃግብር ላይ የክብር አባል ሆኖ እንደሚታደምም ታውቋል።






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: