#Ethiopia | ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ ጎብኚዎች ስለ ሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎች የተሟላ መረጃ በዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚያገኙበት የቨርቹዋል የቱሪስት መረጃ ማዕከል በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች መውጫ አካባቢ ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ።
ፕሮጀክቱን በጋራ ለማስፈጸም የቱሪዝም ሚኒስቴር እና ቶፓን ኢትዮጵያ የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን፣ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ስለሺ ግርማ እና የቶፓን ኢትዮጵያ ተወካይ ቃልኪዳን አረጋ ተገኝተው ሰነዱን ተለዋውጠዋል።
በስምምነቱ መሠረት ለማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገው ወጪ በሁለቱ ተቋማት በጋራ የሚሸፈን ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ የማስፈጸምና የቴክኒክ ኃላፊነት ለቶፓን ኢትዮጵያ መሰጠቱ ተገልጿል።
የቨርቹዋል የቱሪስት መረጃ ማዕከሉ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ጎብኚዎች ስለ ቱሪስት መዳረሻዎች፣ ባህላዊ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ስፍራዎችና ሌሎች የጉዞ አገልግሎቶች መረጃን በቀላሉ እንዲያገኙ በማስቻል የቱሪስት ፍሰትን ለማቀላጠፍና የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ለማጠናከር ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ማዕከሉ በቀጣይ በግንባታ ላይ በሚገኘው አዲሱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ተካቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ዕቅድ መያዙ ተገልጿል።


Source: GetuTemesgen









No comments yet.