የሪል ስቴት ቤቶች የዶላር ገንዘብ መገበያያ ውል ስምምነት አግባብነት

- Advertisement -
Sidebar AD

በኢትዮጵያ ሕግ ማእቀፍ

የዚህ ጹሁፍ መነሻ
#Ethiopia | ለህግ ምክር የመጡ የሪል ስቴት ቤት ተዋዋይ ወገኖች በሰጠውት የህግ ምክር የተነሳ የውል ሰነዶችን ከተመለከትኩት በመነሳት ለማህበረሰቡ የህግ ግንዛቤ እንዲኖረው የቀረበ ነው። ይህ ጹሁፍ በኢትዮጵያ ህግ መሠረት ውልን ለማፍረስ ምክንያት የሆኑ ነገሮች እና አፈጻጸም አስመልክቶ የሪል ስቴት ቤት አቅራቢዎችና ፈላጊዎች መካከል በሚደረጉ የውል ስምምነቶች የሚታዩ ጉድለቶች እና ውጤቶችን በተመለከተ የሚገልጽ በመሆኑ ለመነሻ እውቀት የሚረዳ በመሆኑ ለእናንተ ቀርቦላቸዋል።

1. የሪል ስቴት ውል በኢትዮጲያ በዶላር መዋዋል ይቻላል?

የሪል ስቴት አቅርቦት ውል አስመልክቶ የትኛውንም የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ ሁለቱም ወገኖች በኢትዮጵያ ውስጥ ያደረጉ ኢትዮጵያዊ እስከሆኑ ድረስ የመገበያያ ገንዘቡ በኢትዮጵያ ገንዘብ ሊሆን የሚገባ ነው። ይህ የኢትዮጵያ ገንዘብ መገበያያን አስመልክቶ አግባብነት ያለውን መመልከት የሚቻል ነው። ይህ እስከሆነ ድረስ የተጠቀሰው ገንዘብ የትኛውንም ቢሆን በኢትዮጵያ ገንዘብ/ብር/ ነው ተብሎ ይገመታል። በውሉ ላይ ምንም እንኳን ዶላር ወይም ፓውንድ ተብሎ ቢጠቀስ እንኳን ግልጽ የሆነ የተዋዋይ ስምምነት ፣ ፍትለዊ የሆነ ተጠቃሚነት ፣አንድ ወገንን የማይጎዳ ስለመሆኑ ይህ የገንዘብ መለዋወጫ ካልተተጠቀሰ ፣ካልተብራራ እና አሳማኝ ካልሆነ በቀር
የአንድን ወገን ጥቅም ብቻ የሚጎዳ የውል ስምምነት የሚደረግ ጉዳይ የውለታውን ጉዳይ ሊፈጸም የማይችል ሊያደርገው ይችላል።

2. የተዋዋይ ጥቅምን የሚጎዳ የውል ስምምነት

ተዋዋይ ወገኖች እርስ በእርሳቸው ወደውና ፈቅደው የውል ስምምነት ማድረግ እንደሚችሉ ይህም በተዋዋይ ወገኖች መካከል
ህግ መሆኑን የፍትሀብሔር ህግ ቁጥር 1731 ላይ ተደንግጎ ተቀምጧል። ይሁን እንጂ አንዱ ወገን አግባብ ባልሆነ መንገድ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል የሌላውን ተዋዋይ ወገን ጥቅም በመጉዳት የስምምነቱ አካል የሚሆኑ ሀረግ፣ወይም የውል ድንጋጌዎች ውሉ እንዲፈርስ ወይም እንዲሰረዝ ሊያደርገው ይችላል።

3. በአንድ ወገን ብቻ ተዘጋጅተው ፊርማ የሚደረግባቸው የውል ስምምነቶች

በተቋማት እና በግለሰቦች መካከል የሚጀረጉ ውሎች ለምሳሌ ያህል በኢንሹራንስ ድርጅቶች እና በኢንሹራንስ ተጠቃሚዎች መካከል ፣ በባንኮችና በደንበኞች መካከል የሚደረጉ ውሎች በቤት አቅራቢ ድርጅትና በደንበኞች መካከል፣በመንግስት ልማት ድርጅት/አገልግሎት አቅራቢ እና በበአገልግሎት ተጠቃሚ መካከል የሚደረጉ ውሎች ብዙውን ጊዜ የራሱን ፖሊሲ/ፍላጎት ብቻ በማንጸባረቅ የደንበኛውን ተዋዋይ ሚዛናዊ ጥቅም ባልጠበቀ መልኩ ሲደረጉ የሚስቸዋል ሲሆን ይል ከአጠቃላይ የውል መርሆች አንጻር ሲታይ የተዋዋይ ወገኖችን ፍቃድ እና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ጋር የሚጻረር ሲሆን ብዙ ጊዜ ይስተዋላል።

4. ለውል ስምምነት መፍረስ የሆኑ ምክንያትና የቤት አቅርቦት ውሎች በንጽጽር

4.1 የፍቃድ ጉድለት የፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 1696
ውል በአንደኛው ተዋዋይ ወገን ተንኮል ወይም የሀይል ማስገደድ
ከሆነ ውሉ ፈራሽ እንደሆነ በህጉ ተቀምጧል። ይህ የተንኮል ድርጊት ወይም ሀሳብ በውሉ ባይደረግ ተንኮል የተደረገበት ሰው ውሉን የማይዋዋል ቢሆን ኖሮ ውሉ ፈራሽ የሚሆን ነው።/1704/የሪል ስቴትት አቅራባው በዶላር ውሉን ማድረጉ ዶላር እየጨመረ በመምጣቱ ደንበኛው ተዋዋይ የሚቀረውን ክፍያ ወደፊት ለመክፈል በሚያደርግበት ጊዜ የዶላር ምንዛሬው እየጨመረ ሲመጣ ቤት አቀራቢው እአላግባብ እንዲጠቀም የሚያደርግ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ቤት ፈላጊው ተዋዋይ ይህ በዶላር ክፍያው በመደረጉ ምክንያት የሚመጣበትን ጉዳት ቢያውቅ ኖሮ ውሉን አያደርግም ያስብላል ። ይህም በዚህ ውል ተጎጂ የሆኑ ሰወች ለህግ ምክር ፍለጋ ሲጠይቁን እየተረዳነው ያለው መሠረታዊ ነጥብ ነው። ከዚህ አግባብ ይህ ውል ተንኮል ያለበት የተዋዋይ ወገን ፍቃድ ጉድለት ያለው በመሆኑ ፈራሽ ውል ነው ለማለት እንችላለን።

4.2 ተዋዋይ ወገንን ለመጉዳት ተብሎ የተደረገ ውል
የፍትሀብሔር ህግ አንቀጽ 1710/2/

ይህ ድርጊት አንዱን ተጎጂ የሆነውን ተዋዋይ ወገን ለመጉዳት ሲባል የንግድ ልምድ እውቀት የሌለው መሆኑን በመረዳት ሌላኛው ወገን ይህ ውል እንዲደረግ ምክንያት ከሆነ እና ይህም ከህሊና አንጻር ሲታይም ግፍ መስሎ የሚታይ ከሆነ ለውሉ መፍረስ ምክንያት በቂ ነው። ወደ ሪል እስቴት ቤት አቅርቦት ውልም ስንመጣ የቤት ፈላጊዎች ተዋዋይ ወገኖች ግልጽ የሆነ የንግድ ልምድ እወቀት የሌላቸው ሲሆን የዛሬ አራት አመትና ከዚያም በላይ ወይም የዛሬ በነበረ የዶላር ቤት አቅርቦት ውል በዶላሩ መጨመር አቅራቢዎቹ ቤት ፈላጊውን በመጉዳት የሚደረገው ውል ስምምነት ለህሊና ግፍ ተብሎ በፍርድ ቤት ሲታመንበት ውሉ ፈራሽ ይሆናል።

4.3 በውሉ ሊገለጽ የሚገባው የውለታው ጉዳይ አስፈላጊ ነገሮች
የፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 1713

ውሎች አስገዳጅነታቸው ተዋዋይ ወገኖች በውላቸው ያስቀመጡትን መብትና ግዴታ ብቻ የሚታይ ሳይሆን ያለውን ልማድ፣ቅን ልቦና፣ፍትህ፣የውለታው ነገር ጭምር በመታየት የሚፈጸም እንደሆነ ይደነግጋል። በቤት አቅርቦት በሚደረጉ ውሎች ቤት አቅራቢው የመገበያያ ገንዘቡን የፍትሀብሄር ህጉን አንቀጽ ላይ የተቀመጠውን የኢትዮጵያን ገንዘብ መሆኑን በግልጽ እየታወቀ የዶላርን የወደፊት መጨመርን በማሰብ በተግባርም ሲታይ ዶላር ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ ውሎችም በልማድ መገበያያ ገንዘብ ብር በመሆኑ እንዲሁም ቅንነት እና ፍትህን ያላገነዘበ ውል በመሆኑ ፈራሽ ነው።

4.4 ህግንና ሞራልን የሚቃረን ውል ፈራሽ ነው።
የፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 1716

የዚህ ድንጋጌ ይዘት አንድ ህግ በግልጽ የተደነገገን ህግ የሚቃረን ከሆነ ፈራሽ ነው እንዲሁም ሞራል፣መልካም ጠባይን የሚቃረን ከሆነ ፈራሽ ነው በማለት ያስቀምጣል። ከሪል ስቴት ውሎች በዶላር መገበያያው መደረጉ በፍትሃብሔር ህግ አንቀጽ 1749 ላይ መገበያያው በኢትዮጵያ ብር እንደሆነ የሚያስቀምጥ በመሆኑና እና በስምምነቱ መገበያያው በዶላር መሆኑን ማስቀመጣቸው ህግን የሚቃረን በመሆኑ ፈራሽ ነው ማለት ነው።

4.5 የገንዘብ መገበያያው እዳው በሚከፈልበት ቦታ ባለው ነው
የፍትሀብሄር ህግ ቁጥር 1749

በውሉ ሊከፈል የሚገባው የገንዘብ መገበያያ ሀገሪቱ ላይ ሊከፈል
በሚችለው በሀገሪቱ ህጋዊ መገበያያ ገንዘብ ነው። የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ ብር ሲሆን ዶላር በማድረግ የተደረገው ህገወጥ ሲሆን ውሉን ለመፈጸም የክፍያው ቦታ በኢትዮጵያ እስከሆነ ድረስ መገበያያው በኢትዮጵያ ብር ተደርጎ ሊከፈል እንደሚገባ በፍተሀብሔር ህግ ቁጥር 1750 ከመደንገጉም በተጨማሪ በሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ አዋጅ ቁጥር 1357/2017 አንቀጽ 11 መሠረት በወቅታዊ የገበያ ዋጋ ጥናት ተደርጎ ክፍያው እንደሚፈጸም ይደነግጋል። ስለዚህ በዶላር የሚደረገው የቤት አቅርቦት ውል ስምምነት ህገወጥ በመሆኑ እዳው በሚከፈልበት ጊዜ ባለው የሀገሩ ዋጋ ልክ የሚከፈል ይሆናል እንጂ በስምምነቱ ላይ በተገለጸው የዶላር ዋጋ አይከፈልም ማለት ነው።

5. ማጠቃለያ ሀሳብ እና የጸሀፊው የህግ ምክር

በቤት አቅራቢዎችና ቤት ፈላጊዎች መካከል የሚደረጉ ውሎች
ከመከናወናቸው በፊት ሁለቱም ወገኖች የህግ ባለሙያ በማማከር
የተዘጋጀውን ውል ስምምነት ረቂቅ ለጠበቃና የህግ አማካሪ በማሳየት ቢቻል በመወከል ቦታው ድረስ በመሄድ ህጋዊ የውልል ሀሳቦችን በመለዋወጥ ውሉን በጋራ በማዘጋጀት ማከናወን ያስፈልጋል። አስቀድሞ የህግ ባለሙያ ባለማማከር ብዙ ሰወች በሚሊየኖች ገንዘብ አጥተዋል። በዚህ ጹህፍ ማጠንጠንኛ ሀሳብ የውሉ መገበያያ ገንዘብን ዶላር ያደረጉ ተዋዋዮች የቤት ፈላጊውን ጥቅም የሚጎዳ እና ህጋዊ ባለሆነ ገንዘብ የተደረገ ውል ሲሆን የቤቱ እዳ በሚከፈልበት ጊዜ ያለው ዋጋ ወጥቶ የሚቀረውን ክፍያ በመክፈል እንዲፈጸም በማድረግ የተዋዋይ ወገኖችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እና የኢትዮጵያ ህግ መሠረታዊ ውሎች መርሆችና ድንጋጌዎችን የሚጠበቅ ሲሆን ከዚህ ባሻግር ግን የቤት ፈላጊ ተዋዋይ ወገኖችን ጥቅም የሚጎዳና ህገወጥ በመሆኑ ውሉ ፈራሽ ይሆናል። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ መታየት ያለበት ነጥብ ውሉ ሲፈርስ ተዋዋይ ወገኖች የሚመለስላቸው ገንዘብ በኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ ከሆነ ከምንዛሬ መውደቅ የተነሳ ሊጎዱ ስለሚችሉ በነበሩበት መመለስ ውል ሲፈርስ የኢትዮጵያ ፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 1808 መሠረት ዶላራቸው ተመልሶ ወደ ነበሩበት ቢመለሱ የተሻለ ይሆናል። ለህግ ግንዛቤ ይህንን አልን እንጂ ይህ ልዩ ውል ፣ የህግ ጸባይ በመሆኑ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ተዋዋይ ወገኖች መብታቸውን ለማስጠበቅም ሆነ እንደዚህ አይነት የውል ሴምምነት ውስጥ ለመግባት በዚህ ላይ ልዩ እውቀት ያለውን የህግ ባለሙያ ማማከር ከብዙ ኪሳራ እና ጉዳት የሚጠብቅ ነው።

ማጣቀሻ/references/
1. የኢትዮጵያ ፍትሀብሄር ህግ
2.ሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ አዋጅ ቁጥር 1357/2017

ፋንታሁን ደለለው ጠበቃና የህግ አማካሪ 0929101037
https://t.me/Fantahunlawyer
tiktok.com/@fantahun62395
https://www.facebook.com/share/1HQQwJTrj2/


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: