ታሪክ ይፈርዳል ሕዝብ ይመሰክራል እውነት ለዘላለም ይኖራል!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | እኔ ለኢትዮጵያ የተወለድሁ በኢትዮጵያ ያደግሁ ለኢትዮጵያም ሕይወቴን ለመስጠት በቃልኪዳን የቆምኩ ኩሩ ወታደር ነበርኩ ።

ወታደርነት ዩኒፎርም መልበስ ወይም መሣሪያ መታጠቅ ብቻ አይደለም ። ወታደርነት ማለት የሀገርን ክብር በነፍስ መጠበቅ የሕዝብን ተስፋ በደም ማቆየት የነፃነትን አደራ በትውልድ ላይ ማስቀጠል ነው።
ወታደር ማለት ሀገር ነው።
ሀገር ደግሞ በካርታ ላይ የተሳለ ድንበር ወይም ዝም ያለ መሬት አይደለችም።

ሀገር ማለት የአባቶች አደራ የእናቶች እንባ የጀግኖች መስዋዕትነት የሕፃናት ፈገግታ የወጣቶች ሕልም የአረጋውያን ተስፋ እና የመጪው ትውልድ እጣ ፈንታ ናት።
ሀገር ማለት
• የሕዝቧ ዘላቂ ሰላምና ደህንነት
• የሕፃናት ያልተቋረጠ የነፃነት ሳቅ
• የእናቶች የልብ እፎይታ
• የወጣቶች ብሩህ ተስፋ
• በነፃነት የሚተነፈስ አየርና በፍትሕ የሚገነባ ነገ ናት።

እነዚህን ሁሉ ክቡር እሴቶች በደሙና በሕይወቱ ዋጋ የሚጠብቀው ወታደር ነው። ለእያንዳንዱ የሰላም ሰከንድ የማይታይ መስዋዕትነት አለ ከእያንዳንዱ የነፃነት ቀን ጀርባም የብዙ ጀግኖች ደምና ታሪክ ተጽፎበታል።

ዛሬም ሀገሬ ኢትዮጵያ በጠራችኝ ጊዜ ሁሉ ከፊት የመቆም ግዴታዬን እየተወጣሁ እገኛለሁ። በብሔራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ስለ ሰላም ስለ አብሮነት ስለ ሀገራችን ቀጣይነት ስለ ፍትሕና ልማት ስለ ትውልድ የሚተርፍ አንድነት ከወገኖቼ ጋር በኃላፊነትና በቅንነት እየተመካከርኩ ነው።

ዛሬ ሁላችንም በታሪክ ፊት ቆመናል።
በዚህ ወሳኝ ወቅት የምንናገረው ቃል የምንወስነው ውሳኔ የምንፈፅመው ተግባር በዘመናት መዝገብ ላይ ይቀረፃል።
ስለዚህ ከልዩነታችን በላይ የሚያስተሳስረንን ሀገራችንን እናስቀድማለን ።

ከጊዜያዊ ክርክር በላይ ዘላቂ ሰላምን እንመርጣለን ከመከፋፈል ይልቅ መተባበርን እናከብራለን።
የሕዝብን ተስፋ ለማደናቀፍ የመግባባትን መንፈስ ለማዳከም የሚሞክሩ ድምፆች ሊኖሩ ይችላሉ
ነገር ግን እውነት ከአሉባልታ ይበልጣል አንድነት ከመከፋፈል ይበረታል የሕዝብ ፍቅር ከጥላቻ ይልቃል።

እኛ ኢትዮጵያውያን ነን።
የልዩነታችን ውበት አንድነታችንን አያጠፋም ይልቁን ያጎለብተዋል።
ሰላምን በጽናት ፍትሕን በብልህነት ሀገርን በፍቅር እንገነባለን።

ለኢትዮጵያ የሕይወት ቃልኪዳን
“ሀገሬ ኢትዮጵያ ሆይ!
ለአንቺ የማልከፍለው ዋጋ የማልሰጥሽ ጥረት የማልከብርሽ ክብር የለም።
በጠራሽኝ ጊዜ ሁሉ በየትኛውም ስፍራና በየትኛውም ዘመን ለነፃነትሽ ለሰላምሽ ለአንድነትሽ እና ለክብርሽ እቆማለሁ።
ይህ የፖለቲካ ቃል አይደለም ።
የሕይወቴ ቃልኪዳን ነው።

ይህ የዛሬ ውሳኔ ብቻ አይደለም ። ለመጪው ትውልድ የተቀመጠ አደራ ነው።
አሉባልታ ይጠፋል
ውሸት ይደበዝዛል
ጊዜ ያልፋል
ነገር ግን የታሪክ እውነት የሕዝብ ፍቅር የሀገር ክብር እና የጀግኖች መስዋዕትነት ለዘላለም ይኖራሉ ።
ታሪክ በቃላት አይገነባም በመስዋዕትነት ይጻፋል።
ሀገር በምኞት አትፀናም በአንድነት ትቆማለች።

ሕዝብ በፍርሃት አያድግም በተስፋ ያብባል።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ፍቅር በልጆቿ ጥረት በልጆቿ አንድነት ለዘላለም ፀንታ ትኑር !

ለሐገሬና ለሕዝቤ የተገባ የሕይወት ቃልኪዳን ።

አለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ኢትዮጵያ)



Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: