ኢትዮ-ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል በተመሰረተ በአጭር ጊዜ ወደውጭ ሀገር በሚወስዱ የህክምና ጥገኝነትን በመቀየር፣ በሀገር ውስጥ ዘመናዊ ህክምና መስጠት የሚያስችል አገልግሎት መዘርጋቱን አስታወቀ።
ኢትዮ-ኢስታንቡል አጠቃላይ ሆስፒታል ሐምሌ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በሰጠው መግለጫ ላይ እንደተገለጸው ሆስፒታሉ በመሥራቹና ባለራዕዩ ሲኢኦ አቶ ብርሃን ተድላ እየተመራ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለታካሚዎች ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣ በተለይም በያዝነው 2018 ዓ.ም ብቻ ከ79 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የተመላላሽ ህክምና አገልግሎት በመስጠትና ከ4 ሺ 500 በላይ የቀዶ ህክምናዎችን በማካሄድ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል።
ሆስፒታሉ እነዚህን ሀገር በቀል አቅሞች በመገንባቱ ቀደም ሲል ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር ይሄዱ የነበሩ ታካሚዎችን ቁጥር በመቀነስ የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረት ባሻገር የታካሚዎችን ችግር መቅረፍ ችሏል።
በመግለጫው ወቅት የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር፣ የአጠቃላይ እና ደረት አካባቢ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ተባባሪ ኘሮፌሰር ስዩም ካሣ መርኔ እንደገለጹት፣ ተቋሙ በኢንተርቬንሽናል ካርዲዮሎጂ መስክ ያለ ኦፕሬሽን በደም ስሮች በኩል በሚደረግ ህክምና ጨምሮ በአዋቂና በልጆች የልብ ሕክምና በአጠቃላይ ከ735 በላይ ታካሚዎችን መታደግ ችሏል። አክለውም ይህ አገልግሎት ዓመቱን ሙሉ ሌሊትና ቀን ሳይቋረጥ የሚሰጥ በመሆኑ፣ ከውጭ ሀገር በሚመጡ ጊዜያዊ ዘመቻዎች ላይ ብቻ ጥገኛ የነበረውን አሰራር መቀየር መቻሉን ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በመታገዝ ወደውጪ ሀገር የሚያስኬዱ በተለይ የልብ ሕክምናዎችን 90 በመቶ በሆስፒታሉ መስጠት መቻሉን ጠቅሰዋል።
እንደ ዶክተር ስዩም ገለጻ፣ ሆስፒታሉ በኒውሮሰርጀሪ፣ በኦፕን ካርዲያክ፣ በአጥንትና ስፓይን፣ በኩላሊት፣ በሳምባ፣ የአንጎል፣ የዳሌና የጉልበት ቅየራ እንዲሁም በሚኒማሊ ኢንቬሲቭ (ላፓሮስኮፒክና ቶራኮስኮፒክ) እና ከ46 በላይ ሰብስፔሻሊቲ ህክምና ዘርፎች የላቀ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ የሬዲዮሎጂ ክፍሉም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የህክምና ምርመራ ጥራቱን በማሳደግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
የሆስፒታሉ የውስጥ ደዌና የአዋቂዎች ኢንተርቬንሽናል የልብ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ከፈለኝ ደጀኔ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ከተሰሩት 321 የሕፃናት የልብ ህክምናዎች መከናወናቸውን ጠቁመው 90 የሚጠጋ ድንገተኛ የልብ ደምስር መዘጋት አደጋ ያጋጠማቸውና ታካሚዎች በ24 ሰዓት ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት ህይወታቸው መታደግ ተችላል ብለዋል። ከእነዚህም ውስጥ ቁጥራቸው ከ90 በላይ የሚኾኑ የውጭ ሀገር ዜጎችና ዲፕሎማቶች እንዲሁም ነፍሰጡር እናቶች ይገኙበታል።
የሆስፒታሉ የቺፍ ኦፕሬሽንስ ዳይሬክተር፣ የአንገትና ጭንቅላት ሰብ-ስፔሻሊስት ዶክተር መለስ ገበየሁ እንደገለጹት ደግሞ፣ ተቋሙ ከንግድ ዓላማው ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ ትልቅ ስራ እየሰራ ይገኛል። በሆስፒታሉ ባለቤትና ዋና ስራአስፈጻሚ አቶ ብርሃን ተድላ አማካይነት በተቋቋመው “Heart to Heart Children’s Aid” የተሰኘ ፋውንዴሽን በኩል ትልቅ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
ሜዲካል ዳይሬክተሩ በመጨረሻም ኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደሥራ መግባቱና በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ውጤት መድረስ የቻለው በተቋሙ መስራችና ሲኢኦ አቶ ብርሃን ተድላ የቅርብ ጠንካራ አመራርና ክትትል፣ በሰራተኞችና ባለሙያዎች ትጋት መኾኑን በመጥቀስ ምስጋና አቅርበዋል።
ሆስፒታሉ ለ 333 ጊዜያዊና ቋሚ ሰራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲኾን ከእነዚህ መካከል 86 ያህሉ ሰብስፔሻስት ሐኪሞች መኾናቸው ተነግሯል።




Source: FastMereja









No comments yet.