የኦሮሞን የታሪክና የጥበብ ክፍተቶችን ለመሙላት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ!

- Advertisement -
Sidebar AD

#Fastmereja:የኦሮሞ ምርምር ማህበር(ORA) ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 2ኛው ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ በዛሬዉ ዕለት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል መካሄድ ጀመረ።

“የኦሮሞ የወደፊት ታሪክ፣ እውቀት፣ ባህል እና አስተዳደርን መቀረጽ” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በዚህ ኮንፈረንስ ላይ የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የታሪክ ፕሮፌሰሮችና ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት የተጋበዙ ምሁራን ተገኝተዋል፡፡

የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ እንደገለጹት፤ ማህበሩ የተመሰረተው በኦሮሞ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ ዙሪያ ያሉ የእውቀት ክፍተቶችን በመረጃ ላይ በተመሰረተ ምርምር ለመሙላት መሆኑን አስረድተዋል።

ፕሮፌሰሩ አክለውም፣ ብዙ ጊዜ የኦሮሞ ታሪክ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ብቻ ተደርጎ የሚወራው የተሳሳተ አመለካከት በምርምር ሊታረም እንደሚገባና ህዝቡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሚገባውን ስፍራ እንዲያገኝ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አያይዘዉ ገልፀዋል።

ማህበሩ ከተመሰረተባቸው ያለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ተገልፆ እስካሁን 7 የምርምር መጻሕፍት ለንባብ የበቁ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በሦስት ቋንቋዎች የተዘጋጀውና የፊንፊኔን ታሪክ የሚተነትነው “ፊንፊኔ፡ ትላንትና ዛሬ” (Finfinne: Past and Present) የተሰኘው መጽሐፍ አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።

ማህበሩ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ በገዳ ሥርዓት፣ በኢኮኖሚና ቢዝነስ እንዲሁም በኢሬቻ ላይ የሚያተኩሩ 6 አዳዲስ መጻሕፍትን ለማተም ዝግጅቱን ማጠናቀቁም ተጠቁሟል።

በዚህ ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ኮንፈረንስ ላይ በታሪክ፣ በፖለቲካ፣ በሀገር በቀል ፍልስፍናዎች፣ በአንትሮፖሎጂ፣ በባህልና በቋንቋ ዙሪያ ያተኮሩ 24 የምርምርና ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል። ከእነዚህም መካከል ግማሽ ያህሉ ተመርጠው በመጽሐፍ መልክ እንደሚታተሙ ነዉ የተገለፀዉ።

በኮንፈረንሱ ላይ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከኖርዌይ፣ ከጃፓን፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከአሜሪካ የመጡ ምሁራን በአካልና በበይነ-መረብ እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን የማህበሩ ስራዎች ለኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት ግንባታና በህዝቦች መካከል መከባበር እንዲሰፍን ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ተገልጿል።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: