ኢትዮጵያ ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ግንባታ ከአሜሪካ ተቋማት ጠንካራ ድጋፍ ማግኘቷ ተነገረ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የገንዘብ ሚኒስትር በቢሾፍቱ ለሚገነባው ግዙፍ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት ከአሜሪካ መንግሥት ተቋማት፣ ከታዋቂ የፋይናንስ ተቋማትና ከትላልቅ የኢንዱስትሪ ኩባንያዎች ጠንካራ ድጋፍ ማግኘቱን አስታወቀ ።

ይህ ስምምነት የተገኘው በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደውና ከፍተኛ ውጤት በተመዘገበበት የፕሮጀክቱ የፋይናንስ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ መሆኑ ተጠቁሟል።

የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ላይ ያላቸውን ጽኑ እምነት የገለጹ ሲሆን፣ የ12.5 ቢሊዮን ዶላር የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክትን “አዋጭ እና ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው ኢንቨስትመንት” ሲሉ ገልጸውታል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እንደተናገሩት “የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ያለው ብሔራዊ ቅድሚያ የሚሰጠው ፕሮጀክት ነው፤ ይህም በአፍሪካ እና ከዚያም በላይ ንግድን፣ ኢንቨስትመንትን እና ትስስርን ለማቀላጠፍ ታስቦ የተነደፈ ነው።

በዋሽንግተን የታየው ጠንካራ ተሳትፎ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ያለውን እምነት ያረጋግጣል” ብለዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በበኩሉ እንደገለጸው፤ የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ረዳት ሚኒስትር ሳራ ትራውትማን ከኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱም ትኩረቱን ያደረገው ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን የማቅረብ አቅም ካላቸው የአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር ቀጥተኛ አጋርነትን ማመቻቸት ላይ ነው።

​ቢሮው በትላንትናዉ ዕለት ባወጣው መግለጫ ምክትል ረዳት ሚኒስትር ሳራ ትራውትማን የኢትዮጵያን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እውን ለማድረግ ከሚረዱ የአሜሪካ ኩባንያዎች እና የፋይናንስ አጋሮች ጋር በቀጥታ ለማገናኘት ከገንዘብ ሚኒስትር እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ተወያይተዋል” ብሏል።

ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያን “ቁምነገረኛ የንግድ አጋር” ስትል የገለጸች ሲሆን፤ የአሜሪካ ኩባንያዎች ውስብስብ በሆኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ “ልዩ ብቃት፣ ጥራት እና አጋርነት” ይዘው እንደሚመጡ አስምራበታለች ሲል ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2