ዳሽን ባንክ የ30ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ኤክስፖ ተከፈተ

- Advertisement -
Sidebar AD

​#Ethiopia| ​ዳሽን ባንክ የምስረታውን 30ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀው ልዩ የዳሽን ኤክስፖ በአዲስ አበባ በዋናው መሥሪያ ቤት በድምቀት ተከፍቷል።

ከሚያዝያ 15 እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለዘጠኝ ቀናት በሚቆየው በዚህ ዝግጅት ላይ የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።

ኤክስፖው የባንኩን የሦስት አስርተ ዓመታት የጉዞ ታሪክ፣ ስኬቶችና ከደንበኞች ጋር ያለውን የጠበቀ ትስስር የሚያሳዩ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ለጎብኚዎች ያቀርባል።

​በኤክስፖው መድረክ ላይ ባንኩ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በተለይም በዲጂታል ባንክ አገልግሎት የቀዳሚነት ሚናውን ያረጋገጠባቸው ሥራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የባንኩን የረጅም ጊዜ የንግድ ልምድ፣ ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያለውን ትብብር እንዲሁም በሸሪዓ መርህ የሚመራውን የሰላም ባንክ አገልግሎት ስኬቶችን የሚያሳዩ ዝግጅቶች ተካተዋል።

ባንኩ በፋይናንስ ተደራሽነትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ እያከናወናቸው ያሉትን አዳዲስ አሰራሮችም ለደንበኞቹ በዝርዝር እያስተዋወቀ ይገኛል።

​ከንግድ እንቅስቃሴው ባሻገር ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር መድቦ እያከናወናቸው ያሉ የልማት ተግባራት በኤክስፖው ላይ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።

የአካባቢ ጥበቃ፣ የአረንጓዴ አሻራ እና ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚደረጉ ድጋፎች የዚሁ ዝግጅት አካል ናቸው።

እንዲሁም በኤክስፖው ቆይታ “ደም በመለገስ ህይወትን ያድኑ!” በሚል መሪ ቃል የደም ልገሳ መርሃ ግብር የተዘጋጀ ሲሆን፣ ይህም ባንኩ ለህዝብ ደህንነት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

​በ1988 ዓ.ም በ11 ባለራዕይ ግለሰቦች የተመሰረተው ዳሽን ባንክ፣ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ ከ900 በላይ ቅርንጫፎችና ከ8 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት ቀዳሚው የግል ባንክ ለመሆን በቅቷል።

ባንኩ ከ19 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

📷ከበደ መክብብ
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu #ጌጡ






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: