የቅርብ ጓደኛቸውን በመግደል ሲያሽከረክር የነበረውን መኪና ወስደው የተሰወሩት ሁለት ግለሰቦች ከ23 እስከ 25 ዓመት በሚደርስ

- Advertisement -
Sidebar AD

የቅርብ ጓደኛቸውን በመግደል ሲያሽከረክር የነበረውን መኪና ወስደው የተሰወሩት ሁለት ግለሰቦች ከ23 እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ፡፡

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ/ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ሰሜን ማዘጋጃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል እና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ም/ጠቅላይ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ገ/ሚካኤል ሰይፉ የተባለው ሟች የወንጀል ፈፃሚዎቹ የቅርብ ጓደኛ ነበር፡፡

በዕለቱ ሟች እስከ ምሽቱ 5 ሠዓት ቴዎድሮስ ታከለ እና ሲሳይ ጥላሁን ከሚባሉ ጓደኞቹ ጋር አብሮ ሲዝናና እንዳመሸ የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል።

ወንጀል ፈፃሚዎቹ የቅርብ ጓደኛቸውን አንገት በማነቅ ህይወቱ እንዲያልፍ ካደረጉ በኋላ አስክሬኑን መንገድ ላይ በመጣል ሞባይል ስልኩንና መታወቂያውን ጨምሮ በወቅቱ ሲያሽከረክር የነበረውን የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 4-15624 ኢት መኪና ወስደው ይሰወራሉ፡፡

ፖሊስ የወንጀሉ ሪፖርት ከደረሰው በኋላ ባደረገው ያልተቋረጠ ክትትል ወንጀሉን የፈጸሙትን ግለሰቦች በ24 ሰዓታት ውስጥ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል፡፡

ቴዎድሮስ ታከለ ከአየር ጤና አካባቢ የተያዘ ሲሆን ሁለተኛው ተከሳሽ ሲሳይ ጥላሁን ደግሞ ሱሉልታ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል፡፡

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በተከናወነ ምርመራ የማስፋት ስራ የሰረቁትን ተሽከርካሪ በሸገር ከተማ ወለቴ ተብሎ ወደ ሚጠራው አካባቢ በመውሰድ እንዲሸጥላቸው ለአንድ ግለሰብ እንደሰጡት በማረጋገጥ መኪናው ከቆመበት ቦታ በምሪት እንዲመለስ ተደርጓል፡፡

ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማስደገፍ በአቃቤ ህግ አማካኝነት ክስ እንዲመሰረት አድርጓል፡፡

ቴዎድሮስ ታከለ እና ሲሳይ ጥላሁን በሰው መግደል እና ከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ቴዎድሮስ ታከለ በ25 ዓመት ሲሳይ ጥላሁን በ23 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡

ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲባል የሚፈፀም ማንኛውም የወንጀል ድርጊት ከፖሊስ ዓይን እና ከህብረተሰቡ የሚሰወር አለመሆኑ ታውቆ ወንጀል ፈፃሚዎች ከመሰል ድርጊት እንዲታቀቡም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አሳስቧል፡፡

Addis Ababa police





Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2