ጠ/ሚ’ሯ የተሾሙሏት ኢትዮጵያ AI በጤና ዘርፍ ላይ ምን ያህል ድርሻ አለው?

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ኢትዮጵያ በሕክምናው ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት ሲፈታተኗት የነበሩትን የባለሙያ እጥረት፣ የምርመራ መዘግየት እና የመረጃ አያያዝ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) እንደ ዋነኛ መፍትሔ መጠቀም ጀምራለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ጊዜያት እንደገለጹት፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለኢትዮጵያ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለማቅረብ የግድ አስፈላጊ መሠረታዊ ግብዓት ነው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት የራጅ ወይም የሲቲ ስካን ውጤቶችን ለመተርጎም ቀናትን አልፎ ተርፎም ሳምንታትን ይፈጅ የነበረ ሲሆን፣ ይህ መዘግየት ሀገራችን ወደ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ አማራጭ እንድትመለከት አስገድዷታል።

በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በራሷ ባለሙያዎች የበለጸጉ እና ከነባራዊ ሁኔታዎቿ ጋር የተቃኙ የAI መተግበሪያዎች ባለቤት መሆን ችላለች።

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ያበለጸገው “መላ” የተሰኘው መተግበሪያ በዘርፉ የታየ ትልቅ እመርታ ነው።

መተግበሪያው ፈጣን የምርመራ ውጤቶችን በመስጠት የሳንባ ነቀርሳን (TB) እና የሳንባ ምችን (Pneumonia) ከራጅ ምስሎች ላይ በሰከንዶች ውስጥ በመለየት ለሐኪሞች የውሳኔ ድጋፍ ይሰጣል።

ከዚህ በተጨማሪ የጡት ካንሰር ምርመራ የራጅ (Mammography) ምስሎችን በመተንተን የሕመሙን ምልክቶች በከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት የመለየት ተግባር ያከናውናል።

ካንሰርን ገና በጅምሩ ለመለየት ያለው አቅም የብዙዎችን ሕይወት ለማዳን ወሳኝ ሚና የሚጫወት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በሌላ በኩል የደረት ራጅ ምስሎችን በማንበብ የሳንባ ነቀርሳና ቲቢን የሚለየው ቴክኖሎጂ (CXR-based Diagnosis) የራጅ ባለሙያዎች በሌሉባቸው አካባቢዎች ፈጣን ውሳኔ ለመስጠት እያስቻለ ነው።

ይህ አገልግሎት በየካ ኮቲቤ አጠቃላይ ሆስፒታል እና በተመረጡ የክልል ሆስፒታሎች ተግባራዊ ተደርጓል።

የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ (Cervical Cancer Screening) በምስል ትንተና አማካኝነት ምልክቶችን ቀድሞ መለየት የሚያስችል ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታልና በአንዳንድ የጤና ጣቢያዎች በሙከራ ሂደት ላይ ይገኛል።

በተመሳሳይ የልብ ምትን (ECG) በመተንተን የሕመም ዓይነቶችን የሚለየው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) መተግበሪያ የልብ ስፔሻሊስቶች በሌሉባቸው ሆስፒታሎች ለጠቅላላ ሐኪሞች እንደ ረዳት መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው።

እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በዋናነት በመንግሥት ከፍተኛ የሪፈራል ሆስፒታሎች የተጀመሩ ቢሆንም፣ ቀስ በቀስ ወደ ሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የጤና ሚኒስቴር በቅንጅት እያከናወኑት ያለው ይህ ተግባር የምርመራ ጥራትን በማሻሻል የሀገራችንን የጤና አገልግሎት ወደ አዲስ ከፍታ እያሸጋገረው ይገኛል።

ማስታወሻ ፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው ተሹመዋል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu via#ebc
#Ethiopia #AIinHealth #HealthTech #DigitalHealth #MelaAI #EthiopianAIInstitute


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2