በአዲስ አበባ የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል ስቴት ኤክስፖ ተከፈተ

- Advertisement -
Sidebar AD

​#Ethiopia | ​በኢትዮጵያ የሪል እስቴት አልሚዎች ማህበር አዘጋጅነት “አዲስ አፍሪካ ሪል እስቴት ኤክስፖ 2026” የተሰኘውና በአህጉር ደረጃ የመጀመሪያ የሆነው ታላቅ የኤግዚቢሽን እና የንግድ መድረክ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም በይፋ ተከፍቷል።

ከሚያዝያ 15 እስከ ሚያዝያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ አራት ቀናት የሚቆየው ይህ ኤክስፖ፤ የኢትዮጵያን የሪል እስቴት ዘርፍ ከአህጉራዊ የንግድ ትስስር ጋር በማስተሳሰር አዲስ አበባን በአፍሪካ የዘርፉ የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

​በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አለማየሁ ከተማ ማህበሩ ከተመሰረተ አንድ ዓመት ቢሆነውም ከ100 በላይ አባላትን ማፍራት መቻሉን ጠቁመው፤ ማህበሩ የአባላቱን መብት ከማስጠበቅ ባለፈ ደንበኞች ጥራት ያለውና በውል በተገባው ጊዜ የሚረከቡትን ቤት እንዲያገኙ የሚያስችል የክትትልና የሙያ ስነ-ምግባር ደንብ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በኤግዚቢሽኑ ላይ የሚሳተፉት የማህበሩ አባል የሆኑ ህጋዊና እውቅና ያላቸው አልሚዎች ብቻ በመሆናቸው፣ ቤት ፈላጊው ማህበረሰብ ካልተገባ እንግልት እና ማጭበርበር እንዲጠበቅ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።

​የማህበሩ የቦርድ ሴክሬተሪ ጀነራል ኢንጂነር ዝናቡ ተበጀ በበኩላቸው፤ ይህ ኤክስፖ በተለይ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያለውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለሙ የቴክኖሎጂ አማራጮችና የመንግስት ፖሊሲዎች የሚዳሰሱበት መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኢንጂነሩ ገለጻ አዲሱ አዋጅ ቁጥር 1357/2017 አፎርደብል ወይም ተመጣጣኝ ቤቶችን ለሚያቀርቡ አልሚዎች የመሬት አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ ልዩ መብቶችን የሚፈቅድ በመሆኑ፣ ዘርፉ ለሰፊው ማህበረሰብ ተደራሽ እንዲሆን በር ይከፍታል።

በተጨማሪም በዘርፉ የሚታየውን የቤት ርክክብ መዘግየት እና ማጭበርበር ለመከላከል ከአሁን በኋላ የቤት ሽያጭ በዝግ ሂሳብ (Block Account) እና በስራ አፈፃፀም ሂደት ላይ ተመስርቶ እንዲከናወን መደረጉ የተጠያቂነት ስርዓትን እንደሚያሰፍን ኢንጂነር ዝናቡ አብራርተዋል።

​ይህ አህጉራዊ መድረክ የኢትዮጵያ አልሚዎች ወደ ውጭ ሀገራት ወጥተው እንዲሰሩ መንገድ የሚከፍት መሆኑም ተመላክቷል።

ኢንጂነር ዝናቡ አክለውም የቡርኪና ፋሶ ከፍተኛ ባለስልጣናት በኤክስፖው ላይ መገኘታቸውንና ኢትዮጵያውያን አልሚዎች በዚያ ሀገር እንዲያለሙ ግብዣ መደረጉን ገልጸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ አዲሱ አዋጅ የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ ቤት እንዲገዙ የሚፈቅድ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

​በኤግዚቢሽኑ ላይ ከ30 በላይ የሪል ስቴት አልሚዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና የኮንስትራክሽን ድርጅቶች እየተሳተፉ ሲሆን፣ የሁለተኛው ቀን መርሃ-ግብር የአፍሪካ ሪል ስቴት ማህበር (AFRES) የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ጉባኤን በኢሊሊ ሆቴል በማስተናገድ የሚቀጥል ይሆናል።

ከንግድ ትስስሩ ባለፈም የውጭ ሀገር እንግዶችና ባለሀብቶች በአዲስ አበባ የተገነቡ አዳዲስ የቱሪስት መስህቦችን እና የኮሪደር ልማቶችን እንዲጎበኙ በማድረግ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም እድገት የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል።

ጌትነት ተመስገን
📷 ከበደ መክብብ
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu #ጌጡ






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1