የሰውነት ክብደትን በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጥነት ለመቀነስ መሞከር ለሀሞት ጠጠር መፈጠር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ያውቃሉ?

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የሀሞት ጠጠር የሚከሰተው በሀሞት ከረጢት ውስጥ የሚገኘው ፈሳሽ ኬሚካላዊ ሚዛኑን ሲያጣ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በተለይም በፈሳሹ ውስጥ ያለው የኮሌስትሮል መጠን ከልክ በላይ መጨመር እና የሀሞት ከረጢት ፈሳሹን በአግባቡ ማፍሰስ አለመቻል ለጠጠር መፈጠር ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው።

ጠጠሩ መጠኑ እየጨመረ ሲመጣ ወይም የሀሞት ትቦን ሲዘጋ፤ በላይኛው የሆድ ክፍል ላይ ድንገተኛና ከባድ ሕመም፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እንዲሁም የቆዳ ወይም የዓይን ቀለም ቢጫ መሆንን የመሳሰሉ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል።

የሀሞት ጠጠር ተጋላጭነትን ለመቀነስ ምግብን በሰዓቱ መመገብ፣ ጤናማ የሰውነት ክብደትን መጠበቅ እና ፋይበር ያላቸውን እንደ አትክልትና ፍራፍሬ ያሉ ምግቦችን ማዘውተር አስፈላጊ መሆኑ ይመከራል።

በተለይም የሰውነት ክብደትን በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጥነት ለመቀነስ መሞከር ለሀሞት ከረጢት ጠጠር መፈጠር ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ልዩ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።

የሀሞት ጠጠር በብዙዎች ዘንድ የሚታይ የጤና እክል ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ታካሚዎች ሰፊ ቀዶ ጥገና ሳያስፈልጋቸውና ከፍተኛ ሕመም ሳይሰማቸው መታከም የሚያስችላቸው ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ መዋሉን ዶ/ር ሱራፌል ሙላቱ ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል።

የሕክምናው ዘርፍ በደረሰበት ከፍተኛ እድገት የላፓሮስኮፒክ ወይም በካሜራ የታገዘ ቀዶ ጥገና ለታካሚዎች ፈጣን ማገገምን ይዞ መጥቷል።

ቀደም ሲል የነበረው የሀሞት ከረጢት ቀዶ ጥገና ከ7 እስከ 8 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ሰፊ የሰውነት ክፍልን በመክፈት የሚከናወን ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ይህ አሠራር ተቀይሮ በዘመናዊው የላፓሮስኮፒክ ዘዴ ከአንድ ሴንቲ ሜትር ባነሰ አነስተኛ ቀዳዳ ቀዶ ሕክምናውን በብቃት ማከናወን ተችሏል ነው ያሉት ዶ/ር ሱራፌል።

ይህ ዘመናዊ አሠራር ታካሚው ከቀዶ ህክምናው በኋላ በሰዓታት ውስጥ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው እንዲመለስ ያስችለዋል።

በተጨማሪም ቀዶ ህክምናው በጣም በትንሽ ቀዳዳ ስለሚከናወን በሰውነት ላይ የሚተወው ጠባሳ እጅግ አነስተኛ ነው።

በመጨረሻም ዶ/ር ሱራፌል፤ በጠጠር ምክንያት ጉዳት የደረሰበትን የሀሞት ከረጢት በቀዶ ጥገና በማውጣት ታካሚው ጤናማ ሕይወቱን መቀጠል እንደሚችል አረጋግጠዋል ሲል ኤ ኤም ኤን ዘግቧል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2