የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ እስከ ሰኔ 30 ድረስ የሚፈጸምን ማንኛውንም የመንግሥት ተቋማት ግዢን አገደ

- Advertisement -
Sidebar AD

የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ ምንም ዓይነት ግዢ እንዳይፈጽሙ ዕገዳ መጣሉን አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ዕገዳው የተላለፈው በተለይ ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ባለው የአራተኛው ሩብ ዓመት የበጀት ዘመን የሚፈጸሙ አላስፈላጊ ግዢዎችን ለመግታትና የመንግሥትን በጀት ከብክነት ለመታደግ ነው።

ኃላፊው አክለውም፤ የከተማ አስተዳደሩ ለዘንድሮው በጀት ዓመት ከመደበው ጠቅላላ በጀት ውስጥ 72 በመቶው ለካፒታል ሥራዎች የሚውል መሆኑን አስታውሰዋል። የመንግሥት ተቋማት የሚፈጽሙት ማንኛውም ግዢ በዕቅድ ላይ የተመሠረተና ሥርዓትን የተከተለ ሊሆን እንደሚገባ የገለጹት አቶ አብዱልቃድር፤ በአራተኛው የበጀት ሩብ ዓመት የሚደረጉ ግዢዎች ግን ለብክነት የሚዳርጉ መሆናቸው ቀደም ካሉ ልምዶች በመታየቱ ውሳኔው መተላለፉን አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ ዕገዳው በሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጫና የሚፈጥር መሆኑ ታምኖበት በተቋማቱ ጥያቄ ሲቀርብ፣ ቢሮው ሁኔታውን መዝኖ ግዢው እንዲፈጸም በተለየ ሁኔታ ሊፈቅድ እንደሚችል ኃላፊው ጠቁመዋል። ይህም የሥራ ዕንቅፋት እንዳይፈጠርና አስፈላጊ አገልግሎቶች ሳይስተጎሉ እንዲቀጥሉ ለማድረግ የታለመ መሆኑ ተገልጿል።

አሐዱ


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1