አንጋፋው ሰዓሊና ቀራጺ መጋቢ ጥበባት ሃይለማርያም ሰንበታ ከዚህ አለም ድካም አረፉ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የኢትዮጵያ ሰዓሊዎችና ደራሲዎች ማህበር መስራች አባልና የኢዮቤልዩ ቤተመንግስት ሰዓሊ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የስዕልና ቅርጻቅርጽ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ የነበራቸው መጋቢ ጥበባት ሃይለማርያም ሰንበታ ከዚህ አለም ድካም አርፈዋል፡፡

ቀብራቸውም ዛሬ በደብረሊባኖስ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም ተፈጽሟል፡፡

ከአባታቸው ከአቶ ሰንበታ በዳኔ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፋይቱ ዶዮ በቀድሞ አጠራር በሰላሌ አውራጃ ኢደቡ አቦቴ ወረዳ ስሬ ሞረሴ ቀበሌ ገበሬ ማህበር በ1921 ዓ.ም የተወለዱት መጋቢ ጥበባት ሃይለማርያም ሰንበታ በለጋ ዕድሜያቸው ስሬ መድሃኔአለም አለቃ ጥበቡ ገሜ እግር ስር የቤተክርስቲያን ትምህርት ተከታትለዋል፡፡

ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁም ከአዲስ አበባ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ልደታ ቤተክርስቲያን የዲቁና ማዕረጋቸውን አግኝተዋል፡፡

መጋቢ ጥበባት ሃይለማርያም ሰንበታ ዲቁናቸውን ካገኙ በኋላ በጀሊሳ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ለበርካታ አመታት በላቀ መንፈሳዊ ልዕልና ቤተክርስቲያኑን በዲቁና አገልግለዋል፡፡
መጋቢ ጥበባት ሃይለማርያም ሰንበታ ቤተክርስቲያንን በዲቁና ብቻ ያገለገሉ አባት አልነበሩም፡፡

ከፈጣሪ የተሰጣቸው የስዕል እና የቅርጻቅርጽ ጥበብ ባለቤትም ነበሩ፡፡ መምህራቸው የነበሩት የስሬ መድሃኔአለም ገዳም መምህር አለቃ ጥበቡ ይህንን መክሊታቸውን በማየት ለዚያን ጊዜው ዲያቆን ለአሁኑ መጋቢ ጥበባት ሃይለማርያም ሰንበታ የቤተክርስቲያን ስዕልና ቅርጻቅርጽ ትምህርት አስተምረዋቸዋል፡፡

ይህ የጥበብ ሙያቸው ከቤተክርስቲያን አገልግሎታቸው ጋር ተደምሮ ከትውልድ ሃገራቸው አልፎ በሃገርአቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አድናቆትንና ተፈላጊነትን ስለፈጠረላቸውም ከ1949 ዓ.ም ጀምሮ ወደአዲስ አበባ እንዲመጡ ተደርጎ በታላቁ ገነተ ልዑል ቤተመንግስት በቋሚነት ተቀጥረው ከሌሎች የሃገራችን ታላላቅ ሰዓሊያን ጋር ለ12 ዓመታት በከፍተኛ ትጋትና ታማኝነት የቤተመንግስቱ ሰዓሊ ሆነው አገልግለዋል፡፡

ለጥበብ ስራዎቻቸውም ከተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦችና ንጉሳውያን ቤተሰቦች እውቅናና ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡

በቤተክርስቲያን የነበራቸውን የበርካታ ዘመናት አገልጋይነትና በተለይም በቤተክርስቲያን ጥንታዊ ስዕሎችና ቅርጻቅርጾች ላይ ያሳረፉትን የላቀ አሻራ ከግምት በማስገባትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለረጅም ዘመን የክህነት አገልግሎትና የጥበብ አዋቂነት የምትሰጠውንና ከፍተኛ የሆነውን የ “መጋቢ ጥበባት” ማዕረግ ሰጥታቸዋለች፡፡

የመጋቢ ጥበባት ሃይለማርያም ሰንበታ ታማኝነት፣ ታታሪነትና የቤተክርስቲያን አስተዋዕጾ እጅግ ያስደነቃቸው የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሰነገስት አጼ ሃይለስላሴ በዚያው ገነተ ልዑል ቤተመንግስት በተካሄደ ስነስርዓት በራሳቸው እጅ የንጉሰነገስቱን የክብር ሽልማት ሰጥተዋቸዋል፡፡

መጋቢ ጥበባት ሃይለማርያም ሰንበታ በሃገራዊ የጥበብ ታሪክ ላይ የነበራቸው አሻራ በዚህ ብቻ የሚቋጭ አይደለም፡፡ በጊዜው በነበረው የጽህፈት ሚኒስቴር ስር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውንና ለበርካታ አመታት የሃገሪቱን የጥበብ ሰዎች ሲያሰባስብ የኖረውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሰዓሊያን እና ደራሲያን ማህበር ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌና መቶ አለቃ ለማ ጉያን ከመሳሰሉ የሙያ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን መስርተው በታታሪነት አገልግለዋል፡፡

መጋቢ ጥበባት ቀድሞ በዲቁና ሲያገለግሉበት የነበረው ጀሊሳ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ካህን የነበሩትን የመምሬ ገብረስላሴ ልጅ ወይዘሮ ከበቡሽ ገብረስላሴን አጭተው በ1947 ዓ.ም በዚያው ቤተክርስቲያን ጋብቻቸውን ፈጽመዋል፡፡

መጋቢ ጥበባት ከወይዘሮ ከበቡሽ ጋር በነበራቸው የረጅም አመታት የትዳር ዘመን 14 ልጆችን ወልደው ለወግ ለማዕረግ በማብቃት 27 የልጅ ልጆችንና 8 የልጅ ልጅ ልጅ አይተዋል፡፡

ከሚወዷቸው ባለቤታቸው ህልፈተ ህይወት በኋላ ብዙም ጤና ያልነበራቸው መጋቢ ጥበባት ሃይለማርያም በተወለዱ በ97 ዓመታቸው ሚያዝያ 23 ቀን 2018ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተው ቀብራቸው ሚያዝያ 25 ቀን በታላቁ የደብረሊባኖስ ገዳም ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በታላቅ የቤተክርስቲያን ስነስርዓት ተፈጽሟል፡፡






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1