በ180 ሺህ ዶላር ወጪ የተገዙ የልብ ሕክምና መሣሪያዎች ለሦስት የሕክምና ተቋማት ተበረከቱ

- Advertisement -
Sidebar AD

#FastMereja I የኢዮብ ተስፋ ለሕፃናትና ለወጣቶች በጎ አድራጎት ድርጅት፣ በዛሬው ዕለት ከ180 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ ግምት ያላቸው የልብ ሕክምና መሣሪያዎችንና ቁሳቁሶችን ለጥቁር አንበሳ፣ ለቅዱስ ጳውሎስ እና ለሕፃናት ልብ ማዕከል አስረከበ።

በአመ‍ኤሪካ ካሊፎርኒያ ምዝገባ ያለውና በወጣቱ ኢዮብ አበባው መታሰቢያነት የተቋቋመው ይህ ድርጅት፣ ድጋፉን ያበረከተው በሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ቀዶ ጥገና የሚጠብቁ ሕሙማንን ሕይወት ለመታደግ ነው። ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 28 ቀን 2026 ዓ.ም በተከናወነው የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ፣ ለልብ ቀዶ ጥገና ወሳኝ የሆኑ የፔስሜከር፣ የስተርናል ሳው እና የኦክስጂኔተር መሣሪያዎች ለተቋማቱ ተላልፈዋል።

ድርጅቱ ከተቋቋመባቸው ያለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ በልብ ሕመም ለሚሰቃዩ ሕፃናትና ወጣቶች ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል።

እነዚህ ቁሳቁሶች በሕክምና መሣሪያዎች እጥረት ምክንያት የልብ ቀዶ ጥገና ለማድረግ ተራ ይጠብቁ ለነበሩ በርካታ ሕፃናት ፈጣን ሕክምና እንዲያገኙ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተገልጿል።

ድርጅቱ ቀደም ባሉት ዓመታትም የቬንትሌተር ማሽኖችን ከጀርመን በመግዛት እና የቶንሲል ሕመምን ተከትሎ ለሚመጣ የልብ ቫልቭ መጥበብ ሕክምና የሚረዱ “ኢንዩ ባሉኖችን” በማቅረብ የሕይወት አድን ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በቀጣይም በሕክምና፣ በትምህርት እና በምግብ ረገድ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች አስታውቀዋል።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2