#Ethiopia | በመዲናዋ አዲስ አበባ በማሳጅ ቤት ስም ተሸፍነው በድብቅ የሥነ-ምግባርና የሕግ ጥሰት በሚፈጽሙ እንዲሁም ፈቃድ ሳይኖራቸው በሚንቀሳቀሱ ጤና ነክ ተቋማት ላይ ሰፊ የቁጥጥር ዘመቻ መጀመሩን የአዲስ አበባ ምግብ እና መድኃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ባደረገው ከፍተኛ ክትትል 4 ሺህ 105 በሚሆኑ ጤና ነክ ተቋማት ላይ ድንገተኛ ፍተሻና ቁጥጥር ያደረገ ሲሆን፣ በዚህም በርካታ ግድፈቶች መገኘታቸው ተገልጿል።
የምግብና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ እስጢፋኖስ ጌታቸው እንደገለጹት፤ በርካታ ሕገ-ወጥ ማሳጅ ቤቶች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን (ኮንዶሚኒየሞችን) እና የውስጥ ለውስጥ ሰፈሮችን እንደ መደበቂያ በመጠቀም ፈቃድ ሳይኖራቸው ተግባራቸውን ሲያከናውኑ ተደርሶባቸዋል። እነዚህ ተቋማት ከማሳጅ አገልግሎት ባለፈ “ከባህል ያፈነገጡ” እና ሕገ-ወጥ የሆኑ ድርጊቶችን በድብቅ ሲፈጽሙ እንደነበር ተጠቁሟል።
በቁጥጥሩ ወቅት ደንብና መመሪያ ጥሰው በተገኙ ተቋማት ላይ ባለስልጣኑ የሚከተሉትን እርምጃዎች ወስዷል፦
211 ተቋማት፦ ጠንካራ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
18 ተቋማት፦ ሙሉ በሙሉ እንዲታሸጉ ተደርጓል።
229 ተቋማት፦ እንደ ጥፋታቸው ደረጃ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስዶባቸዋል።
ባለስልጣኑ ይህን እርምጃ የወሰደው የህዝብን ጤና ለመጠበቅና የከተማዋን ሰላምና ስነ-ምግባር ለማስከበር እንደሆነ ገልጿል። በተለይም ፈቃድ ኖሯቸው ከተሰጣቸው የስራ ዘርፍ ውጪ የሚንቀሳቀሱ እና በድብቅ የሚሰሩ ተቋማትን ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት ጥረቱ እንደሚቀጥል ተመልክቷል።
እንደ መናኸሪያ ኤፍ ኤም ዘገባ ዳይሬክተሩ እንዳሉት ይህ ስራ ውጤታማ እንዲሆን የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው የሚመለከቷቸውን አጠራጣሪና ሕገ-ወጥ ተግባራት ለባለስልጣኑ ወይም ለጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu
#አዲስ_አበባ #ጤና_ቁጥጥር #ማሳጅ_ቤቶች #ሕገ_ወጥ #ኢትዮጵያ #AddisAbaba #Ethiopia
Source: GetuTemesgen









No comments yet.