የብልጽግናን የምርጫ ምልክት ባነር የቀደደው በ5 ወር እስራት ተቀጣ

- Advertisement -
Sidebar AD

​#FastMereja I በወላይታ ዞን ባይራ ኮይሻ ወረዳ የፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ባነርን ቀድዶ የጣለው ግለሰብ፣ በዛሬው ዕለት በዋለው የወረዳው ፍርድ ቤት ችሎት በ5 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት።

​በወላይታ ዞን ባይራ ኮይሻ ወረዳ “ጠካቻ ቀጠና 1” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተሰቅሎ የነበረውን የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ምልክት (የስንዴ ነዶ ባነር) ቀድዶ በመጣል ወንጀል የተከሰሰው አቶ በላቸው ባሳ፣ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎበታል። ግለሰቡ ድርጊቱን በፈጸመበት ወቅት በአካባቢው በነበሩ ሰዎች እጅ ከፍንጅ መያዙን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

​የወረዳው ፖሊስ ባደረገው ፈጣን ምርመራ እና በዐቃቤ ሕግ አማካኝነት በቀረበው ክስ መሰረት፣ ተከሳሹ በ2011 ዓ.ም የወጣውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162 አንቀጽ 158ን መጣሱ ተረጋግጧል። ተከሳሹ በችሎት ፊት የቀረበበትን የጥፋተኝነት ክስ አምኖ ቃሉን ሰጥቷል።

​የባይራ ኮይሻ ወረዳ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ፣ ድርጊቱ ተከሳሹን የሚያርምና ሌሎች መሰል የዴሞክራሲያዊ ሂደቱን የሚያውኩ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ የሚያስተምር መሆን አለበት በማለት ተከሳሹ በ5 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል። ይህ ውሳኔ በምርጫ ወቅት የፓርቲዎችን መብትና ምልክቶች ማክበር አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል።


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1