#Ethiopia | በኢትዮጵያ የትምባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ከነበረበት 5 በመቶ ወደ 4.6 በመቶ ዝቅ ማለቱን የኢፌዴሪ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ የዓለም ከትምባሆ ጭስ ነፃ ቀንን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አገሪቱ የትምባሆ ኢንዱስትሪውን የንግድ ጣልቃ ገብነት በመቋቋም ለሕዝብ ጤና ቅድሚያ በመስጠቷ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቷን ገልጿል።
“ለኒኮቲንና ለትምባሆ ሱሰኝነት አጋላጭ የሆኑ ስልቶችን እናጋልጥ!!” በሚል መሪ ቃል በሚከበረው የዘንድሮው የንቅናቄ መድረክ፤ የትምባሆ ኩባንያዎች ታዳጊዎችን በሱስ ለመጥለፍ የሚጠቀሙባቸውን እንደ ኢ-ሲጋራ (vape) እና የኒኮቲን ከረጢቶች ያሉ አዳዲስ ስልቶችን ማጋለጥ ላይ ትኩረት ተደርጓል።
በመግለጫው ላይ እንደተጠቀሰው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በ55ሺህ በሚሆኑ ተቋማት ላይ የቁጥጥር ሥራ የተከናወነ ሲሆን፣ ግምታዊ ዋጋቸው ከ9.7 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ሕገ-ወጥ የትምባሆ ምርቶች እንዲወገዱ ተደርጓል።
በተጨማሪም አዲስ አበባን ከትምባሆ ጭስ ነፃ የማድረግ ሥራ በሁሉም 11ዱም ክፍለ ከተሞች ተጠናክሮ መቀጠሉ ተጠቁሟል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 8 ሚሊዮን ሰዎች በትምባሆ ሳቢያ ለህልፈት እንደሚዳረጉ ያስታወሰው ባለሥልጣኑ፤ በተለይም ወጣቶች በዘመናዊ መልክና በተለያዩ ጣዕሞች ተቀይረው የሚቀርቡ የኒኮቲን ምርቶችን በማንቃት እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርቧል።
ኢትዮጵያም የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011ን መሠረት በማድረግ ማስታወቂያዎችን የመከልከልና በሲጋራ ፓኬጆች ላይ 70 በመቶ የሚሸፍን የስዕላዊ ጤና ማስጠንቀቂያ የመለጠፍ ሕግን እያተገበረች ትገኛለች።
ይህ የተገለጸው የኢፌዴሪ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ፤ ማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን እና ሌሎች አጋር ተቋማት በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ነው።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu

Source: GetuTemesgen








No comments yet.