#Ethiopia | የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን በሀገሪቱ የሚካሄዱ አዳዲስ የሕክምና ሙከራዎችን ደኅንነት፣ ጥራትና ሳይንሳዊ ታማኝነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ዘመናዊ የፈቃድ አሰጣጥና የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱን አስታወቀ።
ይህ የቁጥጥር ሥራ አዳዲስ መድኃኒቶች፣ ክትባቶችና የሕክምና መሣሪያዎች በሰዎች ላይ ከመሞከራቸው በፊትና በሂደት ላይ እያሉ የሚኖራቸውን አስተማማኝነት ለመከታተል ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከአገር በቀል ሕጎች ባሻገር ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የስምምነት መርሆዎችን መሠረት አድርጎ እንደሚሠራ ገልጿል።
እንደ ባለሥልጣኑ ማብራሪያ ከሆነ የሕክምና ሙከራዎች ከደረጃ አንድ እስከ አራት በሚደርሱ አራት የተለያዩ የምርምር እርከኖች የሚከናወኑ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ደረጃ ላይ የሚሳተፉ ወገኖች ሙሉ ፈቃደኝነትና የስነ-ምግባር መርሆዎች መከበራቸው በጥብቅ ይደነገጋል።
ይህንን ሂደት በአግባቡ ለመምራትና ለመቆጣጠርም ባለሥልጣኑ አራት ቁልፍ ተግባራትን ያከናውናል። እነዚህም የምርምር ማመልከቻዎችንና ፕሮቶኮሎችን በጥልቀት መገምገም፣ መመሪያዎችንና የክትትል ማዕቀፎችን ማዘጋጀት፣ የተሳታፊዎችን ደኅንነት በቅርብ መከታተል እንዲሁም የምርምር ተቋማትን በቦታው ላይ በመገኘት በየወቅቱ መፈተሽን ያጠቃልላሉ።
በተለይም የምርምር ተሳታፊዎችን ደኅንነት ለመጠበቅና ድንገት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ከባድ የጤና እክሎችን በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋቱ ታውቋል።
በዚህ ዘመናዊ የምርምር ቁጥጥር ሂደት ውስጥ በርካታ ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን ሚና የሚጫወቱ ሲሆን፣ ጥናቱን በገንዘብና በሃሳብ የሚደግፉ ስፖንሰሮች፣ ምርምሩን በቀጥታ የሚመሩ ዋና ተመራማሪዎች፣ የምርምር ሥነ-ምግባር ኮሚቴዎችና የጤና ሚኒስቴር በዋናነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ አካላት በቅንጅት የሚሠሩት ሥራ የምርምር ጥራትን ከማስጠበቅ ባለፈ ለኅብረተሰቡ ጤና መሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ዜጎች በእነዚህ የሕክምና ሙከራዎች ላይ መሳተፋቸው አዳዲስ የሕክምና አማራጮችን ቀድሞ ለማግኘት፣ የሕክምና ዕውቀትን ለማሳደግና ለቀጣዩ ትውልድ ጤና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል።
ይሁን እንጂ በማንኛውም የሕክምና ሙከራ ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ዜጎች ከምርምር ቡድኑ ጋር በቂ ውይይት በማድረግ ሊገጥሟቸው የሚችሉ ጥቅሞችና ጉዳቶችን አስቀድመው መረዳት እንዳለባቸው ባለሥልጣኑ ያሳስባል።
ተሳታፊዎች በምርምሩ ሂደት ውስጥ በማንኛውም ሰዓት መረጃ የማግኘትና ጥያቄ የመጠየቅ መብታቸው የተጠበቀ ሲሆን፣ የተሰጣቸውን የሕክምና መመሪያዎች በጥንቃቄ መተግበር እንደሚጠበቅባቸው ተመላክቷል።
የሕክምና ሙከራዎችንና ተያያዥ መመሪያዎችን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን ማግኘት የሚፈልጉ አካላት የባለሥልጣኑን ይፋዊ ድረ-ገጽ መጎብኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ



Source: GetuTemesgen









No comments yet.