#FastMereja I የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሕዝብ መዝናኛና አረንጓዴ ስፍራዎችን ለማስፋፋት የጀመረውን ፕሮጀክት አካል በማድረግ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ያስገነባውን ፓርክ ዛሬ በይፋ አስመርቋል።
ይህ በአስኮ አዲስ ሰፈር የተገነባው ሁለገብ ፓርክ፣ ከዚህ ቀደም የአካባቢውን ነዋሪዎች ለአደጋና ለብክለት ይዳርግ ከነበረ የቆሻሻ መጣያነት ወደ ንጹህና መንፈስን የሚያድስ ስፍራነት የተቀየረ የልማት ፕሮጀክት መሆኑ ተገልጿል።
ፓርኩ የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት ፍላጎት ለማሟላት ተገቢው ጥራት ተሰጥቶት የተገነባ ሲሆን፣ በውስጡ በርካታ ዘመናዊ የአገልግሎት መስጫዎችን አካቷል።
ከእነዚህም መካከል ውብ የውሃ ፏፏቴ (ፋውንቴይን)፣ መደበኛ የእግር ኳስ ሜዳ፣ የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎች፣ የባህልና የኪነጥበብ ዝግጅቶች ማቅረቢያ አምፊ ቲያትር፣ ዘመናዊ ካፌዎች፣ የጁስ ባሮችና የተለያዩ ሱቆች ይገኙበታል። በተጨማሪም ሰፊ መኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ)፣ ንጽህናቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የሻወርና የመጸዳጃ ቤት አገልግሎቶች እንዲሁም ነዋሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የእግር ጉዞ የሚያደርጉባቸው ሰፋፊ መንገዶች ተሟልተውለታል።
የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፓርኩን በይፋ ለሕዝብ ክፍት ባደረጉበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና መላው የከተማዋ ማኅበረሰብ ይህንን ከፍተኛ ወጪና እሴት የተጨመረበትን ሁለገብ መዝናኛ ፓርክ በአግባቡ እንዲጠቀሙበትና የጋራ ንብረታቸው አድርገው እንዲንከባከቡት አደራ ብለዋል።



Source: FastMereja









No comments yet.