“ምስጉን ሰው” የተሰኘው መጽሐፍ በድምቀት ተመረቀ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​የአቶ ታምራት ተመስገንን የሕይወት እና የሥራ ታሪክ የሚተርከው “ምስጉን ሰው” የተሰኘው አዲስ መጽሐፍ ዛሬ ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም በዲ ሊዮፖል ሆቴል በተካሄደ ስነ-ስርዓት በይፋ ተመረቀ።

ሰም እና ወርቅ ሚዲያ እና ኢንተርቴይመንት ባዘጋጀው በዚህ የመጽሐፍ የምረቃ መርሃ-ግብር ላይ የክብር እንግዶች፣ አንጋፋ የሥነ-ጽሑፍ ሰዎች፣ የባለታሪኩ ወዳጆች እና ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶች ታድመዋል።

​መጽሐፉ በጉራጌ ዞን በእንደጋኝ ወረዳ ተወልደው በሊስትሮነትና በሌሎች እጅግ አነስተኛ የጉልበት ሥራዎች ሕይወታቸውን የጀመሩትን የአቶ ታምራት ተመስገንን የትግል ጉዞ በሰፊው ይዳስሳል።

ባለታሪኩ ይህንን ፈታኝ የሕይወት ውጣ ውረድ በፅናት አልፈው ሀገሪቱ ካሏት ታላላቅ የግንባታ ኮንትራክተሮች አንዱ ለመሆን የቻሉ ሲሆን፣ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር በሙያቸው እንዲበቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው በምረቃው ላይ ተገልጿል።

​አቶ ታምራት ከጠንካራ የሥራ ባህላቸው ባሻገር በማኅበረሰባዊ እና በበጎ አድራጎት ሥራዎቻቸውም በሰፊው እንደሚታወቁ በመጽሐፉ ተብራርቷል።

በችግር የተዘጉ ቤቶችን በመክፈት፣ አቅመ ደካሞችን በመደገፍ እንዲሁም ህሙማንን በማሳከም ኃላፊነታቸውን የተወጡ ምስጉን ሰው ናቸው። በተጨማሪም መንገዶችን፣ ቤተ እምነቶችን፣ የሕክምና ተቋማትን እና ትምህርት ቤቶችን በገንዘባቸውና በሙያቸው በመደገፍና በመገንባት ለአገልግሎት እንዲበቁ አድርገዋል።

​ይህ የባለታሪኩን አርዓያነት ያለው ሕይወት አጉልቶ የሚያሳየው “ምስጉን ሰው” የተሰኘው መጽሐፍ፣ በሃያሲና የሥነ-ጽሑፍ መምህር ባዩልኝ አያሌው እንዲሁም በደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ተጽፎ ለንባብ የበቃ ነው።

የሕይወት ታሪክ መጽሐፉ በአምስት ዋና ዋና ክፍሎች እና በአርባ ሁለት ምዕራፎች የተዋቀረ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በሶስት መቶ ሰማንያ ሁለት ገጾች ተቀነባብሮ ቀርቧል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu #ጌጡ






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1