ታሪካዊው የማኅበረ ሥላሴ ገዳም አስገራሚ የከብቶች ሰዋዊ ሥርዓትና ረቂቅ ባህሪይ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ውስጥ የሚገኘውና ታሪካዊው ማኅበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሠረተ አንጋፋ መንፈሳዊ ሥፍራ ነው።

ይህ ገዳም ከተለመደው የእንስሳት ተፈጥሮ በተለየ መልኩ እጅግ በሚያስደንቅ ሥርዓትና ፍቅር የሚመሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የሥላሴ ከብቶች መገኛ በመሆን ይታወቃል።

የገዳሙ አፈ መምህር አባ አማሃ ኢየሱስ ወልደ ሥላሴ እንደገለጹት፣ ላምራስ በመባል በሚጠሩት የገዳሙ መነኮሳትና በእነዚህ ከብቶች መካከል ፍጹም አስገራሚ የሆነ የቃልና የስሜት ግንኙነት አለ።

እረኛ መነኮሳቱ እንስሳቱን የሚመሩት በዱላ ሳይሆን በለስላሳ አነጋገርና በፍቅር ቃና ብቻ ነው።

እነዚህ ከብቶች እረኛው ተመለስ ወይም ቁም ሲላቸው ወዲያውኑ ትእዛዝ ያከብራሉ።

ጥጃዎችን ከእናቶቻቸው ለይቶ ወደ ግጦሽ ለመውሰድ በሚፈለግበት ጊዜ ላምራሱ ወገን እያለ ሦሥት ጊዜ ሲያጨበጭብ ጥጃዎቹ ያለምንም ግርግር በሰልፍ መጓዝ ይጀምራሉ።

በተመሳሳይ ሁኔታ ጥጃዎቹ ወተት ጠብተው ሲጨርሱ አጎዶ ማለትም ማደሪያ በረት፣ ለጉዞ ሲነሱ ጉዞ፣ እንዲሁም መድረሻቸው ላይ ሲደርሱ ሠፈር በሚሉ የሦሥት ጊዜ የጭብጨባ ምልክቶች ብቻ ሙሉ ሥርዓታቸውን ጠብቀው ይንቀሳቀሳሉ።

ይበልጥ አስደናቂው ክስተት ደግሞ በገዳሙ የጸሎትና የቅዳሴ ደወል በሚሰማበት ወቅት በእነዚህ በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት መካከል ፍጹም የሆነ ጸጥታ መስፈኑ ነው።

ሰው እግዚአብሔርን ሲታዘዝ ፍጥረት ሁሉ ደግሞ ሰውን ይታዘዛል የሚሉት አባ አማሃ ኢየሱስ፣ የገዳሙ ሕግና ሥርዓት በሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በእንስሳቱም ላይ በተግባር እንደሚሠራ ይመሰክራሉ።

የማኅበረ ሥላሴ ከብቶች አስገራሚ ታሪክ ፍጥረት ሁሉ በፈጣሪና በሰው ልጅ ፍቅር ሲገራ ምን ያህል ውብ፣ ሰላማዊና ሥርዓታማ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ድንቅና ረቂቅ የሕይወት ምስክርነት ነው።

#ማኅበረሥላሴ #ገዳም #የሥላሴከብቶች #ጎንደር #ተአምር #ኦርቶዶክስ #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa



Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1