በአፍሪካ ከፍተኛ ሥጋት እየፈጠረ ለሚገኘው የቦንዲቡግዮ የኢቦላ ቫይረስ ዝርያ እስከ 2026 ዓ.ም ማጠናቀቂያ ድረስ መከላከያ ክትባትና መድኃኒት ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል አስታወቀ።
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዣን ካሴያ እንደገለፁት፥ በአሁኑ ወቅት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከፍተኛ ወረርሽኝ እያስከተለ ለሚገኘውና እስካሁን ምንም ዓይነት ጸደቀ ክትባት ለሌለው ለዚህ የቫይረስ ዝርያ የሚሆኑ በርካታ እጩ ክትባቶች በሂደት ላይ ናቸዉ ።
የአፍሪካ መሪዎች በቴክኒክና በስትራቴጂክ ደረጃ አስፈላጊውን ኢንቨስትመንት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፥ የሩሲያ ጤና ሚኒስቴር ለዚህ ዝርያ የሚሆን ክትባት አስቀድሞ ማዘጋጀቱን የሚገልጽ መልዕክት እንደላካቸው ጠቅሰዋል። ይሁንና የሩሲያው ክትባት የተዘጋጀው ለዛየር የኢቦላ ዝርያ በመሆኑ፥ ክትባቱ በቦንዲቡግዮ ዝርያ ላይ እንዴት ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ከሩሲያው ጋማሌያ የምርምር ማዕከል ጋር ውይይት እንደሚደረግ የቴክኒክ ቡድናቸው አስታውቋል።
ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ካለፈው ግንቦት 15 ጀምሮ በኮንጎ ቢያንስ 1,077 ተጠርጣሪ ኬዞች የተመዘገቡ ሲሆን፥ 246 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ተገልጿል። በሌላ በኩል ወረርሽኙ ወደ ጎረቤት ሀገራት እየተስፋፋ ሲሆን፥ በኡጋንዳ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ ስምንት ከፍ ማለቱ ተረጋግጧል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ ኢትዮጵያም የኢቦላ ወረርሽኝ ለመከላከል የቅድመ ዝግጅት እና የክትትል እርምጃዎችን እያጠናከረች መሆኑን አስታውቃለች።
የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ እንዳስታወቀው፣ እስካሁን ድረስ በሀገሪቱ ውስጥ የተጠረጠረም ሆነ የተረጋገጠ የኢቦላ ህመምተኛ አልተገኘም።
ሚኒስቴሩ እንዳለው፣ ኢትዮጵያ ወረርሽኙ ከተከሰተባቸው ሀገራት ጋር ቀጥተኛ ድንበር ባይኖራትም፣ ከኢትዮጵያ የህዝብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተቀናጁ የጥንቃቄ እርምጃዎች እየተተገበሩ እንደሚገኙ መግለፁ ይታወቃል።
Via capital

Source: Yeneta Tube









No comments yet.