ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር የቀረቡ በርካታ ነጥቦች ላይ ለውጥ እንዲደረግ መጠየቃቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው፤ ትራምፕ የድርድር ነጥቦቹ የበለጠ እንዲጠናከሩ ይፈልጋሉ። እንደ አዲስ ክለሳ የተደረገበት የድርድር ማዕቀፍም ለኢራን ተልኳል።
አክሲዮስ ባወጣው ዘገባ፤ ከኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር እና ዩራንየም የማበልጸግ ሒደት ጋር የሚያያዙ የድርድሩ ነጥቦች እንዲጠናከሩ ትራምፕ ጠይቀዋል።
ትራምፕ የስምምነቱን ረቂቅ ከተመለከቱ በኋላ ለውጥ እንዲደረግ መጠየቃቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
ትራምፕ እንዲደረግ የጠየቁት ለውጥ ድርድሩን በምን መንገድ ሊቀይረው እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር እና ክምችት ትራምፕ ጠንካራ ለውጥ እንዲደረግባቸው ከጠየቋቸው ነጥቦች መካከል እንደሚገኝበት አክሲዮስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት እነዚህ ለውጦች ድርድሩን በቀናት ሊያራዝሙ ይችላሉ።
ትራምፕ ባለፈው አርብ በዋይት ሀውስ አስቸኳይ ስብሰባ ቢያደርጉም የመጨረሻ ውሳኔያቸው ይፋ አልሆነም።
የስምምነቱ ረቂቅ የትራምፕን ይሁንታ እየጠበቀ እንደነበር ኤኤፍፒ ዘግቧል። የኢራን ባለሥልጣናትም ረቂቁን ማጽደቃቸውን አላሳወቁም።










No comments yet.