#FastMereja I የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎን አስመልክቶ ያዘጋጀውን የቅድመ ምርጫ ትዝብት ሪፖርት ዛሬ ይፋ አደረገ። ፌዴሬሽኑ ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ በምርጫው ከተመዘገቡት አጠቃላይ መራጮች ውስጥ 49.3 በመቶው ሴቶች ቢሆኑም፣ በዕጩነት የቀረቡት ግን 25.8 በመቶ ብቻ መሆናቸውን በመጥቀስ በውሳኔ ሰጪነት ረገድ አሁንም ሰፊ ክፍተት መኖሩን አስታውቋል። የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ገነት ስዩም እንደገለጹት፣ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢያንስ 30 በመቶ የሴት ዕጩዎች ተሳትፎን የሚያረጋግጥ አስገዳጅ የውስጥ ደንብ ሊያወጡ ይገባል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎና የቅድመ ምርጫ ሂደቱን ለመታዘብ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ፌዴሬሽኑ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ባካሄደው ሰፊ የኤስኤምኤስ (SMS) የንቅናቄ ዘመቻ 255 ሚሊዮን መልዕክቶችን በ6 የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ተደራሽ ማድረግ የቻለ ሲሆን፣ በፋና ሬዲዮ በኩልም ከ32 ሚሊዮን በላይ መደበኛ አድማጮች ጋር መድረሱን በሪፖርቱ አመልክቷል። በተጨማሪም በቴሌግራም፣ በፌስቡክ እና በቲክቶክ ማህበራዊ ገጾች አማካኝነት የዲጂታል ሚዲያ ቅስቀሳዎች ተካሂደዋል። በምርጫ ሂደቱ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖር ለማስቻልም 267 የረጅም ጊዜ ታዛቢ አሰልጣኞችን በማሰማራት፣ ለ5,165 የአጭር ጊዜ ታዛቢዎች ደረጃ በደረጃ ስልጠና ተሰጥቷል።
በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ደረጃ ያለውን የሴቶች ውክልና አስመልክቶ የወጣው የቁጥር መረጃ እንደሚያሳየው፣ በኦሮሚያ ክልል ሞጆ ከተማ የሴት ዕጩዎች ድርሻ 71.4 በመቶ በመድረስ ከፍተኛውን ቦታ ሲይዝ፣ በአንጻሩ በሲዳማ ክልል 40 በመቶ ሴት መራጮች ቢመዘገቡም የሴት ዕጩዎች ድርሻ ግን 8.2 በመቶ ብቻ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ሁኔታ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ፓርቲዎች በቂ የሴት ዕጩዎችን በማቅረብ ረገድ ያጋጠማቸውን ድክመት እንደሚያሳይ ሪፖርቱ ይገልጻል።
በቅድመ ምርጫ ሂደቱ ወቅት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የታዩ የጸጥታ ስጋቶች ለመራጮችና ለዕጩዎች ዋነኛ ፈተና ሆነው ማለፋቸው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም የሃሰት መረጃዎች ስርጭት፣ የኢንተርኔት ተደራሽነት ውስንነት፣ የባጀት እጥረትና መዘግየት በታዛቢዎች ስልጠናና ስምሪት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ በሪፖርቱ ተቀስሷል። ፌዴሬሽኑ ያጋጠሙ ችግሮችን መነሻ በማድረግ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ለሚመለከታቸው አካላት የዲጂታል ምዝገባ ስርዓት እንዲሻሻልና ለታዛቢዎች የሚሆን በቂ በጀት በወቅቱ እንዲለቀቅ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል።


Source: FastMereja









No comments yet.