ዕዝራ እጅጉ (ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን)
#Ethiopia | በኒው ዮርክ ለረዥም ዓመታት ነዋሪ የነበሩትና፣ ቀደምት በመሆን አገራቸውን በውጭ ዲፕሎማሲና፣ በተባበሩት መንግስታት ጽ/ቤት ያገለገሉት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በአሜሪካን ሐገር በማገልገል የሚታወቁት ዶ/ ር ግርማ አበበ የካቲት 29 ቀን፣ 2017 ዓም አረፉ።
ዶክተር ግርማ አበበ ከአባታቸው ከአቶ አበበ ወልደማርያም እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ማህደር አስቤ በሐምሌ 28 ቀን፣ 1921 ዓ.ም ኢትዬጵያ ውስጥ ነበር የተወለዱት።
ዶ/ር ግርማ አበበ፣ ገና በወጣትነት ዘመናቸው በአሳዩት የትምህርት ውጤትና ችሎታ፣ በ1943 ዓም. በስብስቴ ነጋሲ ት/ቤት ርዕሰ መምህር ሆነው ካገለገሉ በኋላ፣ ለልዩ ስልጠና ወደ እንግሊዝ አገር ተልከው፣ በሊድስ ዩኒቨርሲቲ እና በለንደን ዩኒቨርሲቲ ተምረዋል።
ከዚያም በኋላ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኒው ጀርሲ፣ ፌይርሊ ዲከንሰን ዩኒቨርሲቲ፣ የድኅረምረቃ ዲግሪያቸውን በኒው ዮርክ ባሩክ ኮሌጅ፣ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል።
ዶ/ር ግርማ አበበ፣ በ1950 ዓም. በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሁለተኛ ሴክሬታሪና ቻርጅ ዲ አፌየርስ፣ በ1951ዓ.ም. በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባበሩት መንግስታት የፖለቲካ ጉዳዮች ክፍል – እንዲሁም፣ በ1958 ዓ.ም በኒው ዮርክ፣ የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ሚሽን የመጀመሪያ ሴክሬተሪና በኋላም ካውንስለር ሆነው አገልግለዋል።
ከዚያም ከ1980 ዓም. ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት የፖለቲካና የዲኮሎናይዜሽን ክፍል ሲኒየር ኦፊሰር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በመቀጠል በምክትል ዳይሬክተርነት ለረዥም አመታት አገልግለዋል።
ዶክተር ግርማ አበበ ከባለቤታቸውና ከልጃቸው ጋር በኒውዮርክ፣ የማንሃተን ክፍለ ከተማ ለረጅም ጊዜ ሲኖሩ ማህበረሰባቸውን በማገልገል በህብረተሰቡ ዘንድ ተወዳጅነትና ከበሬታን አትርፈዋል።
ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው የካቲት 29 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ባለቤታቸው እና ወዳጆቻቸው ባሉበት ወደዘላለማዊ ቤታቸው ተሸኝተዋል።ይህን መረጃ ለተወዳጅ ሚድያ ያደረሱት ደራሲ ንጉሤ አየለ ተካ ናቸው፡፡


Source: GetuTemesgen









No comments yet.