👉 ነገም እንደ ሳምንቱ አዳራሽ ሞልቶ እንዳትመለሱ ከዓለም ሲኒማ እና ከዓለም ሲኒማ ዕና ከሁሉ በጄ ቀድማችሁ ቁረጡ
#Ethiopia | ተመልካች አዳራሽ ሞልቶና ተመልሶ ያያቸው ፣ በስነጽሑፋዊ ፋይዳቸው ሲታዩ ደካማ የሚባሉ ትያትሮች ፣ ብዙ ሺህ ቅጂ የተሸጡ መጻሕፍት ፣ የሙዚቃ አልበሞች ኖረው ያውቃሉ ። ተመልካቹ የጥበብ ሊቅነት ( መዛኝነት ) አይጠበቅበትሞ ። ሊጠበቅበትም አይችልም ። አንድ የማይካደው እውነታ በምንም ምክንያት ይሁን ተመልካቹ ያንን ኪነጥበባዊ ስራ ወዶታል ።
በራሴም ስራ ላይ የሙሉነት ስሜት ከተሰማኝ በእርግጥም ያ ስራ ሙሉ ነው ማለት ነው ። እንከን የለሽ ማለት አይደለም ። እንከን የለሽነት ሰዋዊ አይደለም ። ይበልጡን የራሴ ስለሆነው ስለጽሑፉ ላውራና በዚህ ስራ ልክ ደግሜ ደጋግሜ ያነበብኩትና ያስተካከልኩት ስራ የለም ። የእያንዳንዱ ቀን ማስተካከያ ስራው ላይ ያመጣውን ለውጥ እያየሁት ስለሆነ ድካም አልነበረብኝም ። ለዚህ ሙሉ ድርሻውን የምሰጠው ለመስከረም አበራ ነው ። የጽሑፉን ጉድለት ነቅሶ ማውጣትና ማስተካከያ ሀሳብ ማመንጨት እንደ ትወናው ሁሉ ተሰጥዖዋ ነው ። የተሟላ ትወናዋ ከረቀቀ የገጸባህሪ ትንተናና መረዳቷ ይመነጫል ። ዓይኗ የተዋናይ ብቻ ሳይሆን የአዘጋጅም ነው ።
ሸዋፈራሁ ደሳለኝ በየሳምንቱ ትንግርት የሚፈጥርብኝ ተዋናይ ነው ። በእኔ ስራ ላይ ስላገኘሁት እጅግ ደስተኛ ነኝ ። በባለፈው ረቡዕ ትርዒት ወቅት ተመልካች ቆሞ ነው ያጨበጨበለት ። ይገባዋልም ። ለኮሜዲ ስራ ከቀዳሚዎቹ ተመራጮች መሐል አንዱ ነው ። ” አቶ ሻረው ” የሚባሉትን ” ሴቶች ድክመቶቼ ናቸው ” ባይ ገጸባህሪን በራሱ የአጨዋወት ብቃት በአዲስ ቀለም አምጥቶ ለእኔም ራሱ አዲሱን አቶ ሻረው አሳይቶኛል ። ቸርነት ፍቃዱም መዓዛ ገ/ሕይወትም ኃላፊነታቸውን በብቃት ተወጥተዋል ። የማታወርቅ ታደሰ እኔም ራሴ ከእናንተው እኩል በዚህ ሳምንት ነው የማየው ። ከቸርነት ፍቃዱ ጋር በፍርርቅ ነው የሚሰሩት ። የትያትሩ አዘጋጅ የምታውቁት ዳግማዋ አመለወርቅ ፈይሳ ነው ።
እኔ በራሴ ስራ ላይ ለማስታወቂያ ( ለሽያጭ ) ያልተገባ ቃል አላወጣም ። ስለ ” ከትዳር በላይ ” የምላችሁ ” ምርጥ ስራ ነውና እዩት ” ነው ። ቢያንስ ቢያንስ ለምትከፍሉት ብር ተገቢውን እርካታ ታገኛላችሁ ። የተመልካቹ መብዛት በማስታወቂያ ብቻ ሳይሆን በስራው ምስክርነት የመጣም እንደሆነ ትረዳላችሁ ። እሁድ መክፈቻውን አይተው ረቡዕ ደግመው ሊያዩ የመጡ ሁለት ተመልካቾች ገጥመውኛል ። ለማለት የፈለኩት ” ‘ ከትዳር በላይ ‘ የገጠመው የተመልካች ብዛት የሚገባው ነው ” ነው ።
ያላያችሁ እዩትና ያልተገባ ቃል አውጥቼ ከሆነ ጻፉብን ። ወደፊት የምትገቡት ብቻ ሳትሆኑ ከሁለት በአንዱ ቀን የገባችሁም የተሰማችሁን እዚህ መግለጽ ትችላላችሁ ። ባልተገባ ገለጻ ( ግነት ) ገንዘባችሁን አስወጥቻችሁ ከሆነ አትማሩኝ ።
” ከትዳር በላይ ” ተመልካች ቢጎርፍለት የሚገባው ነው ። ከሁሉም በላይ ምርጧን ተዋናይትና ፕሮዲዩሰሯን መስከረም አበራን ፣ አዘጋጁንና ተዋንያኑን በጽሑፍ የነበረውን ተውኔት ነፍስ ዘርተውበት ለዚህ ክብር ስላበቁልኝ ከልቤ አመሰግናችኋለሁ ። ተውኔት በጽሑፍ እያለ ” ሙት ነው ” ይባላል ። ነፍስ የሚዘሩበት ሌሎቹ ሙያተኞች ናቸው ።
ቴዎድሮስ ተ| አረጋይ


Source: GetuTemesgen









No comments yet.