(በተለይ ለመቐለ ዩኒቨርሲቲ አዲ-ሓቂ ካምፓስ ተማሪዎች)
* * *
ከሁለት ቀናት በፊት ከጓደኞቼ ጋር ሻይ እየጠጣን ስለጊቢ ምግብ ተነሳ። የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለን ካፌ እንበላ ስለነበረው አሰቃቂ የሚባል ምግብ አነሳሁ። በዚያው ስለተማሪዎች “ድምፅ አልባነት” አወራን። ምንም ያህል ሐቅ፣ ብሶት እና ጥያቄ ቢኖራቸው ሰምቶ፣ ከቁም ነገር ቆጥሮ የሚመልስላቸው እንደሌለ አወራን። በቅርቡ የቀን የምግብ ወጪ ከ22 ብር ወደ 100 ብር ቢያድግም፣ ምግቡ አሁን እንደባሰ ነገሩኝ። ተማሪዎች እንደሚታመሙ፣ ሰሚም እንደሌላቸው አወሩኝ። የራሴን ገጠመኞች እና ፍረስትሬሽን አስታውሼ እህህ ስል አመሸሁ።
በኛ ጊዜ በጨጓራ እና ሌሎች ሕመሞች ምክንያት ምሳ ወይ እራት የማልበላባቸው ቀናት በርካታ ነበሩ። በእንጀራ ፈንታ ደረቅ ዳቦ ለመውሰድ ላይሳካልኝ የለመንኩባቸውን ቀናት ሳስብ ቲኔጀሩን ገመቹ እያሰብኩ አሁንም ሆድ ይብሰኛል። ዳቦ ለማግኘት ከክሊኒክ የተፃፈ ማዘዣ መያዝ ያስፈልግ ነበር – ደጋግሜ ጠይቄ የተከለከልኩት ማዘዣ። በዚሁ ቁመት 53-55 ኪሎ ነበርኩ። ስመረቅ የለብሰኩት ሸሚዝ እስከመጨረሻው ተቆልፎ እና ከረባት አስሬበት እንኳን የደረቴን ክፍል ያሳይ ነበር። የምግብ እጥረት!!!
ችግሩን የቻልነው ቻልነው። ያቃታቸው ጓደኞቻችን non-café ሆኑ። Non-caféነት ለብዙዎች ቅንጦት አልነበረም – “ተገደው የገቡበት” ኹኔታ ነበር። ዘግይታ የምትሰጣቸው ትንሽ ብር ግን ከቤት ከሚላክላቸው ብር ጋርም ተጨምራ በቀን ሶስቴ አታበላቸውም። በሰቀቀን፣ በጥንቃቄ ነበር የሚኖረው። አንዳንዴ ብሩ ቀድሞ ያልቃል። ከጓደኛ ምናምን ብድር ይጠየቃል። ማን ኖሮት ያበድራል?
ለብዙዎቹ የሚደርስላቸው ገሬ ነበር። ገሬ አዲ-ሓቂ ጊቢ ውስጥ ላውንጅ ፊት ለፊት የነበረችው ኮንቴይነር ሱቅ ባለቤት ነበር። ገሬ እና ጩጬው ልጁን ልዑልን የማያስታውስ የለም። ለጓደኞቻችን ያለመያዣ ዱቤ የሚሰጠው እና ከረሃብ የሚታደጋቸው ገሬ ነበር። አንዲት ተማሪ ተመርቃ ስትሄድ 14 ሺህ ብር ያልከፈችው የገሬ ዕዳ እንዳለባት ሰምቻለሁ። ሳይከፍሉኝ ሄዱ ብሎ አይጨክንባቸውም። ይሰጣቸዋል። በርካቶች አልከፈሉትም።
ከተመረቅን በኋላ ገሬ ራሱ ይረዳው በነበረ ሰው እንደተካደ፣ ሱቁን እንዳጣ፣ ከጊቢም እንዲወጣ እንደተደረገ ሰማሁ። ሊስትሮነት መስራት ጀምሮ ነበር። በዚያ ዕድሜ አልቻለውም መሰል “አልተሳካልኝም” አለ። ዘበኝነት ተቀጥሮ ነበር። ጦርነቱ መጣ፣ ደመወዝ ተቋረጠ፣ በኋላ እሱም ቀረ መሰለኝ። ያ ሱቅ በዩኒፎርሙ ገብቶ ያግዘው የነበረው ትንሽ ልጁ ልዑልም አድጎ ተመርቆ አንድ ፕሮጀክት ላይ ይሰራ ነበር። ጦርነቱ ሲጀመር ከፕሮጀክቱ ሰዎች ጋር ተሰደደ። በሕይወት መኖሩ የታወቀው ቆይቶ ነው። አሁን ተመልሶ እዚሁ አዲስ አበባ ሥራ ፍለጋ ላይ መሆኑን ሰምቻለሁ።
ያ ለተማሪ የሚራራው፣ ከሰው ቀድሞ ጥሩ ነጋዴ የነበረው ገሬ ዛሬ ችግር ላይ ነው። የገሬ ውለታ ያለባችሁ፣ ዕዳ ብቻ ሳይሆን ያ ቅንነቱ፣ ፈገግታው፣ መስተንግዶው የሚታወሳችሁ የቀድሞ የአዲ-ሓቂ ተማሪዎች . . . ገሬን በቻላችሁት መጠን በማገዝ አለንልህ በሉት። በተለይ ዕዳ የነበረባችሁ ሰዎች፣ የመክፈያ አጋጣሚያችሁ አሁን ነው። ሥራ ያላችሁ ሰዎችም ልጁን አናግሩት።
+251914702914 – ስልኩ ነው።
1000152402957 – የንግድ ባንክ አካውንቱ ነው ገብረሚካኤል ኃይለማሪያም።
ሼር በማድረግ ለመቐለ የጊቢ ወዳጆቻችን እንዲደርስ አድርጉ 🤲
መልካም ምሽት!
የቀድሞ ተማሪ ገመቹ መራራ
Source: FastMereja









No comments yet.