ባለስልጣኑ የ13 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደባቸው

- Advertisement -
Sidebar AD

የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፤ ባሳለፍነው ሳምንት በሁለት ክሶች ጥፋተኛ የተባሉት የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ላይ 13 ዓመት ፅኑ እስራትና 21 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ፍርድ ማሳለፉን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ዘግቧል።

ፍርድ ቤቱ የቀድሞዉ ከንቲባ ካቀረቡት 8 የቅጣት ማቅለያዎች 4ቱን በመቀበል እና አራቱን ዉድቅ በማድረግ ነዉ የ13 ዓመት ፅኑ እስራት የፈረደባቸው።

በዚሁ በእሳቸው መዝገብ ተከሳሽ የነበሩት የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ታርኩ ታመነ በ10 ዓመት ፅኑ እስራት እነ 41 ሺህ ብር ፤ አቶ ታፈሰ ቱናሻ በ8 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እስራትና 51 ሺህ ብር እንዲሁም አቶ ሰይፉ ሌሊሴ የተባሉ ግለሰብ እንደዚሁ በ8 ዓመት ከ5 ወር እና 76 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም በዋለው ችሎት የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ አቃቤ ህግ በረ/ፕ ፀጋዬ ቱኬ ላይ በ488,000 ብር የቤት ቁሳቁስ የተገዛበት ብሎ ላቀረበባቸው ክስ ፍ/ቤቱ ነፃ ናቸው ብሏቸው ነበር።

ነገር ግን ” ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገል በአጠቃላይ 97, 088,965/ ዘጠና ሰባት ሚሊዮን ሰማኒያ ስምንት ሺህ ዘጠኝ መቶ ስልሳ አምስት/ ብር ያለአግባብ እንዲባክን አድርጓል ” በሚል በክልሉ ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ግኝት መነሻ የቀረበባቸው ክስ በኦዲት እና በሰው ማስረጃ መረጋገጡን በመግለጽ በተጨማሪም ያልተገባ ጥቅም የማግኘት ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።

ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት ተከሳሽ ረ/ፕ ፀጋዬ ቱኬ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም በአጠቃላይ 97 ሚልዮን 88 ሺህ 965 ብር የመንግስት ገንዘብ እንዲባክን አድርገዋል እንዲሁም 260 ሺህ ብር ያልተገባ ጥቅም አግኝተዋል በሚል ለሁለቱም ወንጀል ክሶች ተከሰዉ ከታሰሩበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር በድምሩ 13 ዓመት ጽኑ እስራት እና 21 ሺህ ብር ቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

በተመሳሳይ አቶ ታርኩ ታመነ፣ አቶ ታፈሰ ቱናሻ ፣ አቶ ተሰማ ዳንጉሼ እና አቶ ሰይፉ ዴሊሳ የመንግስትን ሥራ በማያመች መንገድ በመምራት፣ በሙስና እንዲሁም በሌሎች ክሶች የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸው የነበረ ሲሆን ለቀረበባቸው ክስ የቅጣት ውሳኔ ማቅለያ እንዲደረግላቸው ያቀረቡትን ዝርዝር ምክንያቶች መካከል ተቀባይነት ያገኙትን በመመልከት ፦

2ኛ ተከሳሽ አቶ ተሰማ ዳንጉሼ በሙስና ወንጀል ክስ 3 ዓመት ጽኑ እስራትና 1 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎባቸው በሁለት ዓመት እንዲታገድ፣

በ3ኛው ተከሳሽ አቶ ታሪኩ ታመነ ተከሰዉ ከታሰሩበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር 10 ዓመት ጽኑ እስራትና 41 ሺህ ብር ቅጣት፣

በ4ኛ ተከሳሽ አቶ ታፈሰ ቱናሻ ተከሰው ከታሰሩበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር 8 ዓመት ጽኑ እስራትና 51 ሺህ ብር ቅጣት

በ5ኛ ተከሳሽ አቶ ሰይፉ ዴሊሳ ተከሰዉ ከታሰሩበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር 8 ዓመትከ 5 ወር ጽኑ እስራትና 76 ሺህ ብር ቅጣት ውሳኔ በማሳለፍ የችሎት ዉሎን አጠናቋል።


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1