የ አሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ሊቀመንበር ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ውጥረትን እንዲያረግቡ አሳሰቡ
የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴናተር ጀምስ ሪሽ በትግራይ ክልል እና በአጎራባች አካባቢዎች ዳግም ግጭት ቢነሳ ‘አስከፊ’ አደጋ ያሰከትላል ሲሉ አስጠነቀቁ። “ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ውጥረትን በአስቸኳይ እንዲያረግቡም” ጠይቀዋል።
ሴናተር ጀምስ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ውጥረት እየጨመረ መምጣቱን እና በሕወሀት አመራሮች የተፈጠሩ ውስጣዊ ክፍፍል ማየሉን ተከትሎ ነው።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት “የማይቀር ይመስላል” “ወታደራዊ ዝግጅቶችም የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሰዋል” ማለታቸው ይታወሳል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አራት ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎችን ‘ከመንግስት ውሳኔዎች ያፈነገጡ’ እና ‘ክልሉን ወደ ውስጣዊ ግጭት የሚጎትቱ’ ተግባራት ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል ከስራ ካገደ በኋላ ውጥረቶቹ ተባብሰዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ቀውሱን ለመቆጣጠር ከፌደራል መንግስት ‘አስፈላጊውን ድጋፍ’ የጠየቀ ሲሆን፣ ህወህት ጥሪውን ውድቅ አድርጓል።
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) 03 መጋቢት 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሶስተኛ ወገን ትግራይ ውስጥ እጁን እንዲያስገባ የተደረገው ጥሪ ለፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አደጋ ነው ሲል አስታውቋል።
የምዕራባውያን ኤምባሲዎች እና የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እና እየጨመረ ያለውን ውጥረት እየተከታተሉ መሆናቸውንና ለሰላም ስምምነቱ ያለቸውን ድጋፍ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ትናንት መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሰጡት ማብራሪያ፤ “ትግራይ ውስጥ ከሚፈጠር ትርምስ እናተርፋለን የሚሉ ብዙ ወገኖች አሉ፤ የኤርትራ መንግሥት አንደኛው እንደሆነ አውቃለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
@seledadotio
@seledadotio









No comments yet.