#ለእሳትነት የቅድስና ማዕረግ የደረሰው አባት

- Advertisement -
Sidebar AD

ታላቁ ሊቅ አርእስተ ሊቃውንት ከሚባሉ አባቶች አንዱ ነው። አባቱ ኤስድሮስ እናቱ ኤሚሊያ ይባላሉ። ባልና ሚስት ከተቀደሰ ትዳራቸው አምስት ወንድና አንድ ሴት ልጅ አፍርተዋል። የሚገርመው እህቱ ቅድስት ማቅሪና ገዳማዊት ስትሆን አምስቱም ወንዶች ጳጳሳት መሆናቸው ነው። የሁሉ የበላይ የሆነው ግን ቅዱስ ባስልዮስ ነው። ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ከሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት አንዱ ነው። የቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊም መምህር ነው። ቅዱስ ባስልዮስ ገዳማዊ ጻድቅ፣ ብዙ ምሥጢር የተገለጸለት ሊቅ፣ የብዙ ምዕመናን አባት፣ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት፣ ብዙ ተአምራት ያደረገና ከከዊነ እሳት ከፍጹምነት የደረሰ ነው። በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳያንን ሆስፒታል ያስገነባ እርሱ ነው።

በርካታ ድርሰቶችም ደርሷል። መጽሐፈ ቅዳሴን ዛሬ በምናውቀው መንገድ ያሰናሰለው እርሱ ሲሆን በርካታ ሥርዓቶች ሰርቷል የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትንም ተርጉሟል። ቅዱስ ባስልዮስ በቂሣርያ ማዛካ ቀጰዶቅያ ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡ በዛም የረጅም ጊዜ ጓደኛው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙን ተዋውቋል፡፡ ሁለቱም በአቴንስ በ342 ዓ.ም አካባቢ ጀምሮ ለስድስት ዓመት ተቀምጠዋል፡፡ ባስልዮስ አቴንስን በ348 ለቆ ወደ ግብጽና ሶርያ ከተጓዘ በኋላ በሀገሩ በቂሣርያ የሕግ ሥራ በመለማመድና የንግግር ችሎታ ሲያስተምር እንደቆየ ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ቅዱስ ባስሊዮስ ጥሩ ተናግሮ የማሳማን ጸጋ የታደለ ነበር፡፡ እርሱ ግን ሕጋዊ የማስተማር ሥራውን ትቶ ሕይወቱን ለእግዚአብሔር ሰጠ፡፡

ይልቁንም በመንፈሳዊ ትምህርት ተስቦ በ350 ዓ.ም በአስተሳሰብ ከእሱ ጋር የሚመሳሰሉትን በክርስትና ሕይወት እንዲጓዙ ወንድሙን ጴጥሮስን ጨምሮ ማሰባሰብ ጀመረ፡፡ አንድ ላይ ሆነው በቤተሰቡ ርስት ላይ አኔዚ አጠገብ ገዳም መሠረቱ፡፡ እኅቱ ማክሪናና ሌሎች ሴቶችም ራሳቸውን ለቅዱስ ተግባር በመነሣት ከባስልዮስ ጋር ይተባበሩ ነበር፡፡ ቅዱስ ባስልዮስና ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ የአርያኒዝም የክህደት ትምህርት የቀጰዶቂያን ክርስቲያኖች እንዳይከፋፍል ሲታገሉ ቆዩ፡፡ በኋላም በትልቅ የጉባኤ ክርክር ከታዋቂ አርያናውያን ቴዎሎጂየንና ተናጋሪዎች ጋር ክርክር ለማድረግ ተስማሙ፡፡ በንጉሥ ቫሌነስ ተወካዮች መሪነት ከተደረገው ክርክር በኋላም ጎርጎርዮስና ባስልዮስ አሸናፊዎች ሆነው ወጡ፡፡

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ባስልዮስ የቂሣሪያን ከተማ አስተዳደር ተረከበ፡፡ አውሳቢየስ ግን በባስሊዮስ ፈጣን ችሎታና ዕድገት በማኅበረሰቡ ባገኘው ተቀባይነት በመቅናት ወደ ነበረበት የገዳም ብቸኝነት ኑሮ እንዲመለስ ፈቀደለት፡፡ ጎርጎርዮስ ግን በዚህም በዚያም ብሎ ባስልዮስን እንዲመለስ አሳመነው፡፡ በዚያች ከተማም ለበርካታ ዓመታት ውጤታማ አስተዳዳሪ ሆነ የተደነቀበትን ሥራ ሁሉ ለአውሳብዮስ ተወለት፡፡ በ362 ዓ.ም አውሳቢዮስ ሲሞት ቅዱስ ባስልዮስ እንዲተካው ተመረጠ፡፡ በዛውም ዓመት የቂሣሪያ ሊቀ ጳጳስ ሆነ፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ ለሃይማኖቱ ቀናኢ የሆነ፣ በስብከቱ የሚታወቅ ደግና ለሰው አዛኝ ነበረ፡፡ በዚያም ወቅት ድርቅ ባስከተለው ረኀብ ምክንያት በግሉ ምግብና የሚጠጣ ነገር በማዘጋጀት ድሆችንና አቅመ ደካሞችን የሚያበላ፣ ሀብቱንም ድሆች እንዲጠቀሙ በነበረበት ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚያድል አባት ነበር፡፡

በገዳማዊ ኑሮ ያሉትን እየረዳንና በዓታቸውን እያጸናን የበረከታቸው ተሳታፊ እንሁን፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444




Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1