#ናፍቆት_ዮሴፍ
#Ethiopia | እናንተዬ እንዴት ናችሁሳ። ኧረ ክራር ኧረ ድምፅ ኧረ ግጥም ኧረ ውበት ተሰናሰሉኮ በስማምዬ። እኔማ ቲጂ ካሳ ወስዳ ሲሳይ በገና የባህል ሙዚቃ ት/ቤት ያስጀመረችኝን የክራር ትምህርት ልቀጥለው ነው!! ደሞ ባለፈው ጊዜ ከድምፃዊ አስቻለው ፈጠነ ጋር ቃለ ምልልስ ስናደርግ “ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ ብቻውን ባንድ መሆን ይችላል እሱን እያቋቋምኩ ነው እኔ 6 አይነት ክራር አለኝ” ሲለኝ እህ ያለ ድራም ያለ ሳክስፎን ያለ ኦርጋን እንዴት ብሎ እያልኩ ልቡን ያወለቅኩትስ ነገር🤔🤔 እኔን ብሎ ሙዚቃ አዋቂ።
አስቼዋ ኧረ የኩኩ ሰብስቤ ” ሳለኝ” ዘፈን ላይ ያለችው ልብ ስልብ የምታደርግ ክራር ከስድስቱ ክራሮችህ የትኛዋ አይነት ትሆን? መልስልኝማ በሞቴ!! ሳለኝ የሚለው የኩኩ ሰብስቤ የዘፈን ግጥምና ዜማ በቴዲ አፍሮ የተሰራ ነው። ግጥሙ አንዴ ሰሜን ጎንደር ጃናሞራ ደረስጌ ማሪያም ሲወስደኝ አንዴ አርባምንጭ ብሔራዊ ፓርክ ሲከተኝ አንዴ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የሚባልን መስሪያ ቤት ሲያስወቅሰኝ ኧረ ተውኝማ አራወጠኝ እንጂ🤔🤔
*ሳለኝ ሳለኝ በልብህ ብራና በፍቅርህ ቀለም
እንዳልጠፋ አድርገህ እስከዘላለም
ስየሃለሁ እኔማ ልቤ ላይ በእንባዬ ነክሬ
ባልነበረ ቀለም ባልታየ እስከዛሬ
ትላለች በዚህ መሐል የክራሩ ድርድር ከኩኩ ድምፅ ጋር ሲዋሃድ አርባምንጭ ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ ያለው ጥርት ኩልል እያለ እየተንሿሿ ቀስ ብሎ የሚወርደውን ከ40ዎቹ ምንጮች አንዱን በዛ መዓት ጫፍ ባለው ቅጠል እየደቀንን የምንጠጣውን ውሃው ጥርት ከማለቱ የተነሳ( ስር ኩል) የሚስለውን ይመስለኛል ድምጿ። ከዛ ስለቀለም ስትቀኝ ድሮ ፊደል ሲቀረፅ ብራና ሲፃፍ ጥቅም ላይ የዋለው ላባ(ላባው የዶሮ ይሁን የጅግራ የማውቅላችሁ ነገር የለም) ብቻ ላባው ይታየኝና የቀለሙን ከለር ለመወሰን እቸገራለሁ ። አሃ ባልነበረ ቀለም ባልታየ እስከዛሬ አለቻ!!
ደረስጌ ማሪያም ውስጥ ያሉ በራስ ውቤ ከየቦታው ተሰብሶበው የተከማቹ አጃኢብ የሚያሰኙ በርካታ ብራናዎች ላይ የተሳሉት ደማማቅ ስዕሎች ታወሱኝ ከተለያዩ ዕፅዋት በተቀመሙ ቀለማት የተሳሉት። ነገር ግን ኩኩ
ከአበቦች ገላ ላይ ቀለም ቢቀመም
ያንተን ውበት ችሎ የሚገልፅ የለም
ብላ የዕፅዋቱን ቀለም አቅመቢስአደረገችዋ!!
ቀለም ቀለም
ያልነበረ ባለም
ውበት ውበት ኤዶማዊ ገነት
እያለች የኔን የመረዳት አቅም ከዜሮ ዲግሪ በታች ስታወርደው ጊዜ እጄን አፌ ላይ ጭኜ አይ ክራር አይ ዘመን አይ ውበት አይ ጥበብ አወይ ድምፅ አወይ ፍቅር ከማለት ውጪ ምን እላለሁ??
ደሞ በተናጠል ወደ ባለቋንቋው ዐይን መጣች። ዐይን ድምፅ ሳያወጣ የሚናገር መልዕክት የሚያስተላልፍ ባለቋንቋ ነው ይሉታል። ደግሞ ስለውበቱ የሚነገርለት ውበት ከሚገለፅበት የአካላችን ክፍል አንዱ ነው አይን።
እናማ ኩኩሻ ሆዬ
ኮከብ መስሎ የሰማይ ላይ ፈርጥ
ክው አረገኝ አይኑ ሲገለጥ
ይነዳል ወይ ዐይንም እንደ እሳት
እያየኸኝ ልቤን አትለኩሳት
እንደሰው አይቀልም አንተን ወዶ መርሳት
በማለት አቅመቢስ ያደረጋትን የአይኑን ውበት ትገልፃለች ። መርማሪ አይን ቀልብ ወሳጅ አይን ታዛቢ አይን በየአይነቱ አለ። የአይን ውበት በዚህ ልክ ሲገለፅ አላጋጠመኝም ወይም አልሰማሁም። ሁሉን ሰምቶ የሚችለው የሚያመዛዝነው ጆሮ ግን መቼ ነው የሚዘፈንለት ማንስ ነው የሚቀኝለት ማንስ ነው የሚያዜምለት? ጆሮ ግን ከአምስቱ የስሜት ሕዋሶቻችን መሐል አንዱ ሆኖ ለሚዳስሰው እጅ ለሚያሸተው አፍንጫ ለሚያየው አይን ቅኔ እንደውሃ ሲፈስ ጆሮ በቅናት አይንጨረጨርም? ታድሎ ትዕግስተኛ ነው ግብዝም አይደለም መሰለኝ።
አፍንጫን ወደሚፈትን ምዕራፍ ዘለቀች ኩኩ እንዲህ በማለት።።
ከከርቤም ያስንቃል ከናርዶስ ከዕጣን
ጠረንህ ደስ ሲል ልክ እንደ ህፃን
መቼስ የፈጣሪ ስራው ድንቅ አይደል? የአራስን ልጅ የአንገት ስር ጠረን ከምን እንደሰራው አላውቅም። እኔ ነኝ ያሉ የፈረንሳይ ሽቶ ቀማሚዎች ሲያምጡ ቢከርሙ የህፃን ልጅ ያንገት ስር መዓዛን የሚያክል አይጥሩም። ከውድ ሽቶዎቻቸው ጋር አይነፃፀርም አያመጡትምም። ኩኩ ሳለኝ እያለች የምታሽሞነሙነው ውብ ሰው መዓዛ ከምን ጋር እንደተነፃፀረ አስቡትና የዚህን ሰው ተፈጥሮ ሳሉት።
አይቆጨኝ ለፍቅርህ ሩሔን ባወርስ
የቀረኝን ዕድሜ ዛሬ ብጨርስ
ኧረ ወየው ምን አይነት ምትሃት ውበት ነው በፈጣሪ? ለማንኛውም ሩሕ ለማታውቁ(ነፍስ)ማለት ነው። ለዚህ ውብ ነፍስ እስከማውረስ ድረስ የሚልቅ ፅኑ ፍቅር ምን መሳይ ነው? አጃኢብ ነው ብቻ። ከኤዶም ገነት የሚፈልቅ ውበት??? አልገብቶኝም እኔ ለራሴ ሆሆ ፈተና ነውኮ እናንተዬ 🤔🤔🤔🤔🤔
አሁንም ወደ ሰሜን ጎንደር ጃናሞራ ደረስጌ ማሪያም ልመልሳችሁ ነው።ለምን በብቻዬን ካገር አገር እንከራተታለሁ?
በፈርጥ እንዳጌጠ የነገስታት ዘውድ
መልክህ አስደንግጦ ልብ የሚያሰግድ
ስትል ልቤ ወደነገስታቱ ዘመንና አገር ሽምጥ ጋለበና ደረስጌ ማሪያም ያየሁትን የነገስታት በርካታ የወርቅ ዘውዶች የወርቅና የብር መቋሚያዎችና መስቀሎች፣ የወርቅና የብር ከበሮዎች በወርቅና በብር ሰንሰለትና መርገፍ ያጌጡትን የነገስታት ካባዎች መልሼ በአይነ ሕሊናዬ ቃኘሗቸው።
በ2009 ዓም የአፄ ቴዎድሮስን 150ኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ በዓል ጎንደር ዩኒቨርስቲ አዘጋጅቶ ነበር። ከዝግጅቶቹ አንዱ አፄ ቴዎድሮስ ከተወለዱበት በክብር እስተሰውከበት ያለውን ቦታ መጎብኘት ነበር። ዕድለኛ ሆኜ ከጎብኚዎቹ አንዷ ነበርኩ። በጉብኝቱ አፄ ቴዎድሮስ ከተወለዱበት ቋራ ጀምሮ ቄስ ትምህርት ቤት የተማሩበት የሸፈቱበት ዋሻ ሳይቀር እስከተሰውበት መቅደላ ድረስ ተጉዘናል ። ከጉዞው ልመስ ጉብኝቱን የሚያስቃኝ ” አፄ ቴዎድሮስን ፍለጋ ከቋራ ስሰከመቅደላ” የሚል የጉዞ ማስታዎሻ በምሰራበት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ማስፈሬን አስታውሳለሁ።ሊንኩን ፈልጌ አጋራችሁ ይሆናል። ደረስጌ ማሪያም ያለውን የሐገሪቷን ሐብትና ቅርስ ያየሁት በዚህ ጉብኝት ነው።
ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልንን ምን አስወቀሰሽ አትሉም?
ራስ ውቤ ከላይ የገለፅኩላችሁን ቅርሶችና ሌሎችንም በርካታ ሐብቶች ከበርካታ ብራናዎች ጋር በደረስጌ ማሪያም ቤተክርስቲያን አጠራቅመዋል። ሊነግሱ ነበራ! ከግብፅ ወጣት ጳጳስ ሁሉ አስመጥተዋል ንግስና የሚቀባቸው። በዚህ መሐል አፄ ቴዎድሮስ ድንገት ጦርነት ከፍተው ራስ ውቤን ማርከውና አስረው ራስ ውቤ ለራሳቸው ባመጧቸው የግብፅ ጳጳስ ንጉሰ ነገስት ተብለው ተቀብተው የራስ ውቤን ልጅ ጥሩዬን(ጥሩወርቅን) አግብተው በስማቸው ማህተም አስቀርፀው ብራናዎቹላይ ማህተም መትተው እነዚህን ቅርሶችሶ አደራ ጠብቃችሁ ያዙ ብለው ወደጎንደር መመለሳቸውን ታሪክ ያስረዳል። ከዛን ጊዜ ጀምሮ የደረስጌ ማሪያም አካባቢ ሰው በደሳሳ ጎጆ ውስጥ ያንን ሁሉ የወርቅ ዘውድ የወርቅ ከበሮ የብርና የወርቅ የቁም መስቀል ምኑን ልንገራችሁ እጅግ በርካታ ሐብት እንቅልፍ እያጣ ሲጠብቅ ኖሮ እካስሁን ዘልቋል። አንድ ፈረንጅ በጉብኝቱ ያንን ሁሉ የወርናነ የብር መዓት ሲመለትከ ” ራስ ውቤ ቤተክርስቲያኗን ሊያገቧት ነበር እንዴ እንደ ዕጮኛ በወርቅ ያንቆጠቆጧት?” ሲል መጠየቁን አስጎብኚያችን ነግሮን ነበር።
የሚገርማችሁ ነገስታቱ የሚለብሱት በወርቅና በብር ወርቀዘቦ መርገፍ የተንቆጠቆጡት ካባዎች በተራ የስፌት አገልግል ውስጥ ነው እንደ አልባሌ ነገር የተቀመጡት።
እናስ ባለስልጣኑ የቴዎድሮስ ቆንዳላ ይመለስልኝ (ለነገሩ ተመልሷል) እንግሊዝ የወሰደችው ጀርመን የሰረቀችው ብራና ሌላም ቅርስ ይመለስልኝ እያለ የሚያባክነውን ጉልበትና ጊዜ ደረስጌ ማሪያም ያለውን ያንን ሁሉ የወርቅና ብር ቅርስ ሙዚየም ሰርቶ በወግ በወጉ ሰድሮ አስተማማኝ ጥበቃ አድርጎ ቅርሶቹን ከጉዳት የአካባቢውን ሰው ከስቃይ አይገላግለውም? እስከዛሬ አገር ሰላም በሆነ ጊዜ ከጎብኚዎች በተለይም ሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ለመጎብኘት ይጎርፍ ከነበረው የፈረንጅ መዓት ልናኝኘ የሚገባንን ጥቅም አላገኘንም። ምክንያቱም የአካባቢው ህዝብ ጠብቁ እንጂ አሳዩ አልተባልንም ይሰረቅብናል በሚል ይከለክል ነበር። ግንዛቤው መፈጠር ሲጀምር የሰላም መደፍረስ ተከተለ። ግዴለም ሐገር ሰላም ይሆናል ሁሉም ነገር እንደነበረ አይቀጥልምና ያ ቅርስ ከፍተኛ ትኩረት ያሻዋል። በጉብኝታችን ወቅት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ለነበሩት ሒሩት ወልደማሪያም(ፕ/ር) ይህንኑ ጥቄ አቅርቤ ነበር።
እዛ ቦታ ላይ ድንቅ ከሚሉኝ ቅርሶች መካከል ከደረስጌ ማሪያም ሲደወል ባርቅ ድረስ የሚሰማው የድንጋይ ደወል ነው። በደባርቅና በጃናሞራ መሐል ያለውን እርቀት ብታዩ በድንጋዩ ደወል ድምፅ ይበልጥ ትደነቁ ነበር። በዕጣን ጭስ የሚሰራውም የአፄ ቴዎድሮስ ማህተም ሌላው ድንቅ የሚለኝ ነገር ነው!!
ቅርስን የጃናሞራ ሰው አብዲ ነጋሽና አቤ ከቤ የአሰላው በየዘርፉ ይጠብቋት ። ዛሬ ምንድነው የነካኝ? ምኑን ከምኑ ነው ያገናኘሁት? ኩኩ ስንቱን አስዘባረቀችኝ?
ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)የነካኸው ይመርልህ ተብለህ የተፈጠርክ ሰው።❤💪🙏 ምን አይነት ብዕር ነው?ምን አይነት ማሰላሰል ነው?ምንአይነት ዘመን መዋጀት ነው የተቸረህ ግን? ብዕርህ አይንጠፍ ጠቢቡ🙏🙏 ኩኩዬ ሳለኝን በዚህ በመረዋ ድምፅሽ ስታንጎራጉሪው ምን ተሰምቶሽ ይሆን? ብቻ እንዲሁ ለጆሯችን ምግብ እንደሆንሽ ኑሪ ውዷ🙏❤💪
ድንቅ ጥምረቶች❤❤
Source: GetuTemesgen









No comments yet.