#Ethiopia | በዘመናዊው የከተማ ኑሮና በስራ ጫና ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች “ተፈጥሮ” ከማንኛውም መድኃኒት በላይ አዳሽና ለጭንቀት መፍትሔ መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ።
በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ (University of Michigan) የተካሄደውና በ “Frontiers in Psychology” መጽሔት ላይ የታተመው አንድ ጥናት፤ በቀን ውስጥ ለ20 ደቂቃ ብቻ ከተፈጥሮ ጋር ጊዜ ማሳለፍ በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የጭንቀት ሆርሞን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ አረጋግጧል።
የጥናቱ ግኝት ምን ይላል?
ተመራማሪዎቹ “የተፈጥሮ ክኒን” (Nature Pill) ብለው በሰየሙት በዚህ ጥናት፤ ሰዎች ስልክ ሳይጠቀሙ፣ ኢንተርኔት ሳይመለከቱ ወይም መጽሐፍ እንኳ ሳያነቡ ለ20 ደቂቃ ብቻ አረንጓዴ ስፍራዎች ውስጥ መቀመጥ ወይም በእግር መጓዝ የጭንቀት መጠናቸውን በ21% እንደሚቀንስላቸው ደርሰውበታል።
ይህ ውጤታማ እንዲሆን ግዴታ ወደ ሩቅ ቦታ መሄድ አይጠበቅብዎትም፤ በአቅራቢያዎ ባለ ፓርክ፣ በጓሮዎ ውስጥ አልፎ ተርፎም ዛፎች ባሉበት መንገድ ላይ በእርጋታ መቆየት በቂ ነው ተብሏል።
ዋናው ነጥብ ግን በእነዚህ 20 ደቂቃዎች ውስጥ ከቴክኖሎጂ መራቅና አእምሮን ከተፈጥሮ ድምፅና ቀለም ጋር ማገናኘት ግድ ይላል።
ጥናቱ ሳይንሳዊ መንገድን ተጠቅሞ ይፋ ቢያደርገውም በርካቶች ዘንድ የተለመደ ተግባር ነው። እርሶ ሞክረውት ያውቁ ይሆን ?









No comments yet.