በጥቁር አንበሳ ባለሙያዎች ህይወቱ የተረፈው ቤቢ መሐመድ

- Advertisement -
Sidebar AD

#FastMereja I በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ገና በ25 ሳምንቱ የተወለደውና ክብደቱ 900 ግራም ብቻ የነበረው ህጻን መሐመድ ዋቢ፣ ከሦስት ወራት ከፍተኛ የህክምና ትግል በኋላ በሙሉ ጤንነት ወደ ቤቱ ተሸኘ።

ሳይንሳዊ ስሌቱ “ውርጃ” ሊባል በሚችልበት ደረጃ ላይ የነበረውን የህጻኑን ህይወት ለመታደግ የሆስፒታሉ የጨቅላ ህጻናት ፅኑ ህሙማን ክፍል (NICU) ባለሙያዎች ያደረጉት ርብርብ ተአምራዊ ውጤት አስመዝግቧል።

ወይዘሮ መኪያ ከማል የተባሉ የ36 ዓመት እናት ባጋጠማቸው ድንገተኛ ህመም ምክንያት ኮልፌ ቀራኒዮ ከሚገኘው ግራር ጤና ጣቢያ ወደ ጥቁር አንበሳ የተላኩት እርግዝናቸው ገና በ25 ሳምንት ከ5 ቀን ላይ እያለ ነበር። ህጻን መሐመድ ዋቢ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሲወለድ ክብደቱ ከአንድ ኪሎ ግራም ያነሰ (900 ግራም) በመሆኑ የመኖር እድሉ እጅግ አነስተኛ ተደርጎ ተገምቶ ነበር።

እንደተወለደ ለ10 ደቂቃ የሚቆይ የልብና የመተንፈሻ ማነቃቂያ የተደረገለት ሲሆን፣ በቀጣይነትም በአወንታዊ የመተንፈሻ ግፊት (CPAP) ድጋፍ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል ገብቷል። የክፍሉ ኃላፊ ሲስተር ጠጄ ቱፋ እንደገለጹት፣ ባለሙያዎቹ ህጻኑን ከመታደግ ባሻገር ተስፋ በቆረጠችው እናት ላይ ሲሰሩ የነበረው የስነ-ልቦና ግንባታ ለውጤቱ ትልቅ ድርሻ ነበረው።

ከታህሳስ 7 ቀን እስከ መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ወራት የዘለቀው ክትትል የሚከተሉትን ውጤቶች አስመዝግቧል፦ ከ900 ግራም ወደ 1.8 ኪሎ ግራም አድጓል። የተደረጉ የዓይን፣ የጆሮ እና አጠቃላይ የአካል ምርመራዎች ህጻኑ ፍጹም ጤነኛ መሆኑን አረጋግጠዋል። ህጻኑ መጋቢት 21 ቀን በደስታ እምባ ታጅቦ ወደ ቤቱ ተሸኝቷል።

ሲስተር ጠጄ ቱፋ አክለውም፣ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን ለመከላከል እናቶች ከእርግዝና በፊትና ወቅት የህክምና ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል ሲል አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ነው የዘገበው።





Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: