ፒራሚድ የተሰኘ የሽያጭ ስልትን በመጠቀም ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅም በማዋል የተከሰሱ ጥፋተኛ ተባሉ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በተከለከለ ‘ፒራሚድ’ የተሰኘ የሽያጭ ስልት ተጠቅመው ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅም በማዋል የተከሰሱ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላለፈባቸው።

ተከሳሾቹ ቲያንስ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር፣ ሚስተር ዶዮንግ ጋንግ፣ አቶ ቴዎድሮስ በቀለ፣ ወ/ሮ ሱዓዳ ሙክታር የወንጀል ሕግ 34/1/1 የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 22/6/ እና 43/2/ ሥር የተደነገገውን የወንጀል ድርጊት በመፈጸም ዐቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በዚህም ቲያንስ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በአስመጪነት የንግድ ስራን ለመስራት የግብር ከፋይ መለያ ተመዝግቦ የአልሚ ምግብ አስመጪነት የንግድ ሥራ ፈቃድ በማውጣት ከ2004 እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት ከውጭ ሀገር የሚያስመጣቸውን መድሐኒት እና የተለያዩ አልሚ ምግቦች ለመሸጥ ለሌሎች ተከሳሾች “የኮሚሽን ሽያጭ ወኪል በሚል ውል በመስጠት፣ በወኪሎች ስር እንዴት አባላት በሽያጭ ሰንሰለት ውስጥ እንደሚመለምሉ ስልጠና በመስጠት፤ የተለያዩ ግብይቱ የሚከናወንባቸውን ቅጾች በማዘጋጀትና ተግባራዊ በማድረግ ተገቢ ያልሆነ የአባልነት ክፍያ እንዲፈጸም አድርጓል።

በድርጅቱ ስም የአባልነት መታወቂያ በማዘጋጀትና ተግባራዊ በማድረግ፤ አባል ያልሆኑ ለግብይት የቀረቡ ምርቶችን እንዳይሸጥላቸው በማድረግ፤ አባል የሆኑት ደግሞ የተለያዩ ተከሳሹ ከውጭ ሀገር የሚያስገባቸውን ምርቶች አስቀድሞ ትዕዛዝ እንደተሰጠ በማስመሰል በስሙ በተመዘገበ የባንክ ሂሳብ ቁጥር በቀጥታ በራሱና በወኪሎቹ አማካኝነት ከፍተኛ መጠን ያለዉ ገንዘብ በመሰብሰብ፤ በዚህም በአባልነት የተመዘገቡት ብዛት ያላቸው ግለሰቦች ወደ ሽያጭ ስልት ውስጥ አስገብቷል።

ለዚህም የተለያዩ ግለሰቦችን በመመልመልና በእነሱ ስር በሽያጭ ሰንሰለቱ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ብዛት ያላቸው ግለሰቦችን በሰንሰለቱ ውስጥ በማስገባት የተለያዩ አልሚ ምግቦችን እንዲገዙ ወይም የገንዘብ መዋጮ እንዲያደርጉ እና በእነርሱ ቀጥሎ ሌሎች ሸማቾች የአልሚ ምግቦች የሚገዙ ወይም የገንዘብ መዋጮ የሚያደርጉ ከሆነ ወይም በሽያጭ ስልቱ የሚገቡ ከሆነ በሚገቡ ሸማቾች ቁጥር ልክ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ጉርሻ፤ የመኪና ሽልማት ወይም የውጭ ሀገር ጉዞዎች እንደሚያገኙ በማስመሰልና ሀሰተኛ ገለጻ በማድረግ፤ የአልሚ ምግቦቹን አሻሻጥ በመወሰን፤ ቅጾችን በማዘጋጀትና ስልጠናዎችን በመስጠት በአጠቃላይ የሽያጭ ስልቱን በመንደፍ በፈጸመው ፒራሚዳዊ የሽያጭ ስልት ተግባራዊ ማድረግ ወይም ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር ወንጀል ተከሷል፡፡

በ2ኛ እና በ3ኛ ተከሳሾች ላይ በቀረበ 2ኛ ክስ ደግሞ ተከሾቹ ከጥር 2006 እስከ ጥር 2008 ዓ.ም ውስጥ የድርጅቱን ጥቅም በሕገ-ወጥ መንገድ ለማራመድ በማሰብ ከላይ በ1ኛ ክስ ውስጥ የተመለከተውን ተግባር 1ኛ ተከሳሽ እንዲፈጽም የመሩ በመሆናቸው በፈጸሙት ፒራሚዳዊ የሽያጭ ስልት ወንጀል ተከሰዋል፡

በ3ኛ ክስ ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 34/1 እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29/2/ለ እና መ ስር የተመለከተውን መተላለፉን ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።

1ኛ ተከሳሽ በ1ኛ ክስ ላይ በተመለከተው ወንጀል አማካኝነት ያገኘውን ገንዘብ ሕገ-ወጥ አመጣጡን ሰውሮ በስራ ላይ በማዋል፣ በማዘዋወር ወይም በባንክ በማስተላለፍ ህጋዊ አስመስሎ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 32 ሚሊየን 739 ሺህ ብር እና በወጋገን ባንክ 7 ሚሊየን 768 ሺህ ብር በድምሩ 40 ሚሊየን 507 ሺህ 996 እንዲቀመጥ እና እንዲንቀሳቀስ በማድረግ ከወንጀል የተገኘ ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሷል፡፡

በ4ኛ ክስ በተመሳሳይ ቀሪ ተከሳሾች በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል።

እንደ ኤፍ ኤም ሲ ዘገባ የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ በ16 ተደራራቢ ክስ በተከሰሱት ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸውን በመግለጽ የጥፋተኝነት ውሳኔን በማሳለፍ፤ ለቅጣት ውሳኔ ለሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #fmc


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1