ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ እና ባለ አክስዮን የማኅበሩ እዳ ተጠያቂነት

- Advertisement -
Sidebar AD

በኢትዮጵያ ህግ ማእቀፍ
ጠበቃና የህግ አማካሪ ፋንታሁን ደለለው

መግቢያ
#Ethiopia | ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በኢትዮጵያ ንግድ አዋጅ እና በሌሎች የህግ ማእቀፎች እውቅና የተሰጠው ሲሆን በሁለት እና ሀምሳ አባላት መካከል የሚደራጅ በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ
የሚሳተፍ የንግድ ማህበር ነው። በዚህ ጽሁፍ የማህበሩን ስራ አስኪያጅ እና የባለ አክስዮኑን ኃላፊነት በማህበሩ እዳ ያለበት ኃላፊነት በተመለከተ እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ግንዛቤ ለማህበረሰቡ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን ጽሁፍ አዘጋጅተን ለእናንተ አቅርብናል።

1. ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ትርጓሜ

የንግድ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 አንቀጽ 495/1/ መሠረት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማለት ዋና ገንዘቡ በሙሉ አስቀድሞ የተከፈለ፣ በአክሲዮን የተከፋፈለ እና ባለአክሲዮኖች መዋጮአቸውን ገቢ እስካደረጉ ድረስ ለማኅበሩ ዕዳ ኃላፊ የማይሆኑበት የንግድ ማኀበር ነው::

2. የባለ አክስዮን ኃላፊነት መሠረታዊ ግዴታ

የባለአክሲዮኖች ኃላፊነት ሲባል በእዳ በማህበሩ እዳ የሚጠየቁበት ጭምር ማለት ነው። ባለ አክስዮኖች የሚጠበቅባቸውን የካፒታል መዋጮ እያንዳንዳቸው ገቢ ካደረጉ በማህበሩ እዳ ሊጠየቁ እንደማይችሉ፣ ራሱ ማህበሩ ሊጠየቅ የሚችል መሆኑን ከላይ ከተቀመጠው አንቀጽ 495 መረዳት የሚቻል ነው። ስለሆነም ከጅምሩ ኃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር የመፍጠር አላማው በማህበሩ እዳ ባለአክስዮኖች እንዳይጠየቁ ማድረግ ነው።

3.የማህበሩ ስራ አስኪያጁ ስልጣን

ስራ አስኪያጅ ከማህበሩ ውስጥ ባለ አክስዮን ሆነም አልሆነም በጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት የሚመረጥ መሆኑን በንግድ ህግ አንቀጽ 514 ላይ ተቀምጧል። ይህ ከሆነ በኋላ በህግና መመስረቻ አግባብ ይሰራ ዘንድ ስልጣኑን መለየት ኃላፊነቱን ለመረዳት ይቻል ዘንድ እንደሚከተለው በአንቀጽ 515 ላይ ተቀምጧል።

ሀ) ማኅበሩ በቦርድ የሚተዳደር ከሆነ ስለስራ አስኪያጅ ሥልጣን በዚህ ሕግ አንቀጽ 337 እስከ 339 የተመለከቱት ድንጋጌዎች እንደ አግባብነቱ ተፈጻሚ ይሆናሉ፤

ለ) ማኅበሩ ቦርድ የሌለው ከሆነ ሥራስኪያጁ የማኅበሩንን ዓላማ ለማሳካት በማኅበሩ ስም ለመስራት ሙሉ ስልጣን ይኖረዋል፤

ሐ) የሥራ አስኪያጁን ሥልጣን የሚገድቡ የማኅበሩ መመስረቻ ጽሑፍ ድንጋጌዎች በማኅበሩ፣ በባለአክሲዮኖች እና በሥራ አስኪያጁ መካከል ካልሆነ በስተቀር ውጤት አይኖራቸውም፡፡ ሲል ይደነግጋል።

4. ባለ አክስዮኖች በማህበሩ እዳ ሊጠየቁ የሚችሉት መቼ ነው?
በንግድ አዋጅ ቁጥር 495/3/ ወሳኝ ድምጽ ያለው ባለአክሲዮን ተጠያቂነትን በተመለከተ በዚህ ሕግ በአንቀጽ 295 ሥር የተደነገገው ተፈጻሚነት እንዳለው ያስቀምጣል። በዚህም መሠረት
ባለአክስዮኖች ለማህበሩ እዳ ተጠያቂ የሚሆሆኑበትን በአንቀጽ 295 ላይ እንደተቀመጠው

አንቀጽ 295 የባለአክሲዮኖች ተጠያቂነት

በዚህ ሕግ አንቀጽ 245 የተደነገገው ቢኖርም፤ ማንኛውም ወሳኝ ድምጽ ያለው
ባለአክሲዮን ከዚህ በታች ከተመለከቱት አንዱን ፈፅሞ ከተገኘ ተጠያቂ ይሆናል፡-

ሀ) የማኅበሩን፣ የባለአክሲዮኖችን ወይም የማኅበሩን ገንዘብ ጠያቂዎችን ጥቅም ጉዳት ላይ የሚጥል ህገ-ወጥ ድርጊት ሆን ብሎ መፈፀም፣

ለ) የማኅበሩን ንብረት ከባለአክሲዮኑ ንብረት ጋር መቀላቀል፣

ሐ) የማኅበሩን እና የባለአክሲዮኑን ማንነት አለመነጣጠል፣ ማኅበሩን ለግል ወይም ለሶስተኛ ወገን ዓላማና ጥቅም እንደ ሽፋን መጠቀም፣

መ) ስለማኅበሩ የፋይናንስ አቋም የማኅበሩ ገንዘብ ጠያቂዎችን ሊያሳስት የሚችል መረጃ ሆን ብሎ ማውጣት፣

ሠ) ከገበያ ዋጋ ባነሰ ክፍያ ወይም አግባብ ካለው የማሕበሩ አመራር ውሣኔ እና እውቅና ውጪ የማኅበሩን ሀብት ለራሱ ወይም ለሶስተኛ ወገኖች የግል ጥቅም ማዋል ወይም

ረ) በሕግ ከሚፈቀደው በላይ የትርፍ ክፍያ መፈፀም፡፡
ይህንን ባለአክስዮኑ በፈጸመ ጊዜ ከማህበሩ ጋር በአንድነት እና በነጠላ ኃላፊነት ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለው ለፈጸመው እዳ ተጠያቂ ይሆናል።

5. የስራ አስኪያጅ ኃላፊነት/ተጠያቂነት/

አንቀጽ 516 የስራ አስኪያጁ ተጠያቂነት
ሀ) ተቃራኒ ስምምነት ቢኖርም ሥራ አስኪያጁ በሕግ ወይም በመመስረቻ ጽሑፍ የተመለከቱ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ለሚያደርሰው ጉዳት ለማኅበሩ፣ ለባለአክሲዮኖች እና ለሦስተኛ ወገኖች ኃላፊ ነው፤

ለ) ማኅበሩ በመክሰሩ ምክንያት ሀብቱ ዕዳውን ለመክፈል በቂ ሆኖ ያልተገኘ እንደሆነ በከሰረው ማኅበር ንብረት ጠባቂ አመልካችነት ፍርድ ቤት የማኅበሩ ስራ አስኪያጅ እና የቀድሞ ሥራ አስኪያጆች የማኅበሩን ዕዳ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲከፍሉ ለመወሰን ይችላል፤

ሐ) የአስተደደር ኃላፊነታቸውን በተገቢው ጥንቃቄና ትጋት መወጣታቸውን ባስረዱ ስራ አስኪያጆች ላይ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) ድንጋጌ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡

ከድንጋጌው መረዳት እንደሚቻለው ስራ አስኪያጁ አግባብነት ያላቸውን ድንጋጌዎች በመተላለፍ ለሚያደርሰው ጉዳት ተጠያቂ ነው።

በተጨማሪም ማህበሩ በመክሰሩ ምክንያት ለሚጠየቀው የማህበሩ እዳ ስራ አስኪያጁ ተጠያቂ ሲሆን አስተዳደሩ በጥንቃቄ በትጋት በህግ አግባብ ማህበሩን የመራ ስለመሆኑ ካስረዳ ከኃላፊነት/ተጠያቂነት የሚድን ይሆናል።

6. የጹሁፉ ማጠቃለያ

ኃላፊነቱ በተወሰነ የግል ማህበር ባለ አክስዮኖች መዋጮዋቸውን ገቢ እስከ አደረጉ ድረስ በመርህ ደረጃ ለማህበሩ እዳ ተጠያቂ አይሆኑም።

ስራ አስኪያጅም ቢሆን ህግን በመጣስ ምክንያት በማህበሩ ላይ ጉዳት እስከአላመጣ ድረስ ለማህበሩ እዳ የሚጠየቅበት አግባብ የሌለ ሲሆነ ማህበሩ ከከሰረ ግን ስራ አስኪያጁ የማህበሩ ሀብት እዳውን ለመክፈል በቂ ካልሆነ እንዲሁም ስራ አስኪያጁ በህግ አግባብ ያስተዳደረ መሆኑን ካላስረዳ ለማህበሩ እዳ ተጠያቂ ይሆናል።

ማጣቀሻዎች/References/
1. የንግድ አዋጅ ቁጥር 1243/2013
2. ፍቃዱ ጴጥሮስ የኩባንያ ህግ በኢትዮጵያ
ጠበቃና የህግ አማካሪ ፋንታሁን ደለለው
0929101037,0983337690


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: