መሬማ ያ የመኒያ

- Advertisement -
Sidebar AD

*********
ታሪክን የኋሊት ስንበረብር ወደ ኢትዮጵያ የገናነት ዘመን ይወስደናል – የአክሱም ዘመነ መንግስት። ኢትዮጵያዊያን ነገስታት ባብል መንደብ (Bab El Mendeb chokepoint) ይቆጣጠሩ ደቡብ ዓረብያ ድረስም ያስተዳድሩ ነበር። ሀገረ ናግራን ብዙ የክርስትና ታሪክ የነበረባት የአክሱም ግዛት አካል ነበረች። የአይሁድ ነገስታት በክርስቲያኖች ላይ ያደርሱ የነበረውን ጭቆና እና ግድያ ለማስቆም የአክሱም ነገስታት ህዝባቸውን ለመታደግ ሰፊ ውጊያ እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር። ከፋርስ (Persia) እና ሃድራሙት ኃይሎች ጋር በተደረጉ ጦርነቶች ሳቢያ የአክሱም ተፅዕኖ በዓረቢያ ላይ ቀነሰ። ከእስልምና መምጣት በኋላ ደግሞ የአክሱም ተፅዕኖና ገናነት በቀይ ባህርና አከባቢው ቀጠና መሸርሸር ዠመረ። የኢኮኖሚ ድቀትንም አስከተለ። በመጨረሻም የአክሱም መንግስት በዮዲት አመጽ ሙሉ ለሙሉ ወደቀ።

ነገረ-መሬማ

ከየመን አጠቃላይ ህዝብ 10% ያህሉ ቀለማቸው ምስራቅ አፍሪካዊ ነው። በዚህም ምክንያት ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተገፎ ከሰው በታች የሆነ ህይወት ለአያሌ ዘመናት በመግፋት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ዜጎች ከቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል በጦርነቱ ሳቢያ ተቆርጠው የቀሩ ሊሆኑ ይሆናል። ቴዎድሮስ ካሳሁን Teddy Afro ለመግለጽ የፈለገውም እነዚህን ጭቁኖች ሊሆን ይችላል – በኔ አረዳድ። ለዛም ነው “ሊብናን ቤሩት ካታር ባህሬን ሳውዲ ዱባይ
እንደሚያዝነው ልቤ እህት ወንድሜን ሳይ” ብሎ የጠይሟን የመኒ ስቃይ ከእህት ወንድሞቹ ስቃይ እኩል ህመም እንደሆነበት የገለጸው።
መሬማ በሰንዓ ከባድ ህይወትን የምትገፋ ክቡር የሰው ልጅ ናት። በሀገሯ ዜጎች የሰውነት ክብር የተነፈጋት ሴት። የመኒዎች ለተራበ አጉራሽ ለታረዘ አልባሽነታቸው በስፋት ሲወራ ብንሰማም ቅሉ፤ በቀለም ለተለዩት የመኒዎች ግን በተቃራኒው እንደሆኑ መሬማ ማሳያ ነች። እኛኑ ኢትዮጵያውያንን የሚመስሉት “እንደ አፋር አፍሌታ” ፊታቸው የጠየመው ምስኪን ህዝቦችን ግን ኑሯቸውን አስከፊ አድርገውባቸዋል። ብቸኛው የገቢ ምንጫቸውም ከተማውን የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ እና ሌሎች ለመስራት የሚጸየፉት መሰል ስራዎችን ነው።
“ጠጋ ብለሽ አውጊኝ እስኪ ያለሽበት ሁኔታውን
እያየሽው በትካዜ የምትጠርጊው ጎዳናውን
አጎንብሰሽ ስትቆዝሚ ተደግፈሽ መጥረጊያውን
አሳዘንሽኝ እኔማ
ስንት አለ ሆድሽ መሬማ” መሬማ እነርሱን ጠይም የመኒዎችን የምትወክል ናት። አምሳያዎቻችን በመልክ እንጂ በቋንቋችን ብንጠራቸው አይሰሙንም። በዘመን ብዛት ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ትስስራችን ደብዝዟል። ለዚህም ነው ቴዲ
“ባያት አምሳያዬን ብጠራት አትሰማ
መሬማ
….
ኑሮሽ ኑሮሽ እንዴት ነው
በሰነዓ ከተማ
ያ መሬማ” ያለው።
የመኒያ ምድር ላይ የፍትህ ጀምበር ስትወጣ እንደሰው እንደዜጋ ክብርን ትጎናፀፊያለሽ ፥ ያ መሬማ።

Via Habtu A nigus

“ሙሀማሺን” (ትርጉሙም “የተገለሉ” ማለት ነው) በየመን የሚኖሩ ቁጥራቸው እስከ 3.5 ሚሊዮን የሚደርስ ጥቁር አናሳ ማህበረሰቦች ናቸው።

እነዚህ ወገኖች ለዘመናት በዘለቀ የዘር መድልዎ በከፋ ድህነት እና በማህበራዊ መገለል ውስጥ ይገኛሉ።

ስለ አመጣጣቸው የተለያዩ መላምቶች ቢኖሩም አብዛኛው የታሪክ ድርሳናት እንደሚጠቁሙት ከ6ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በየመን የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወይም ከምስራቅ አፍሪካ (ሱዳን እና ኢትዮጵያ) የፈለሱ ባሮች ዝርያዎች ናቸው ተብሎ ይታመናል።

ይህ የታሪክ ትስስር ቢኖራቸውም፣
በየመን የማህበራዊ ደረጃ ዝቅተኛው እርከን ላይ ተቀምጠው እንደ “የማይነኩ” (untouchables) ተቆጥረው ይኖራሉ።

ሙሀማሺኖች እምነታቸው እስልምና ቢሆንም እና አረብኛ ቋንቋን የሚናገሩ ቢሆንም ከዋናው የየመን ማህበረሰብ ጋር እንዳይቀላቀሉ ተደርገዋል ይህም አብዛኛውን ጊዜ በዝቅተኛ ስራዎች (ለምሳሌ በፅዳት) ላይ ብቻ እንዲሰማሩ ይገደዳሉ የተሻለ የስራ ዕድልና ትምህርት አይፈቀድላቸውም።

ንጹህ ውሃ የጤና አገልግሎት እና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማግኘት እጅግ ይቸገራሉ።

አብዛኞቹ እንደ ሰነዓ ባሉ ትልልቅ ከተሞች ዳርቻ በሚገኙ የድህነት መንደሮች (Slums) ውስጥ ተፋፍገው ይኖራሉ።

በየመን ለዓመታት የቀጠለው የእርስ በእርስ ጦርነትና ሰብአዊ ቀውስ የሙሀማሺኖችን ሁኔታ ይበልጥ አባብሶታል በጦርነቱ ምክንያት ለከፋ ረሃብና ለልመና የተጋለጡ ሲሆን እርዳታ በሚከፋፈልበት ወቅትም በመገለላቸው ምክንያት የመጨረሻ ተጠቃሚ ወይም ተጠቃሚ የማይሆኑበት ሁኔታ በስፋት ይታያል።

*ምንጭ፦ ቶምሰን ሮይተርስ ፋውንዴሽን ኒውስ (Thomson Reuters Foundation News)*




Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: