የኢራኑ ተደራዳሪ ለተጨማሪ ምክክር ወደ ፓኪስታን ተመለሱ

- Advertisement -
Sidebar AD

የኢራኑ ተደራዳሪ ለተጨማሪ ምክክር ወደ ፓኪስታን መመለሳቸው ተዘገበ።እንደ አሶሸትድ ፕሬስ ዘገባ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ዛሬ እሁድ ለተጨማሪ ምክክር ወደ ኢስላማባድ ተመልሰዋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የልዑካናቸውን የፓኪስታን ጉዞ ቢሰርዙም ዓለም አቀፍ አስታራቂዎች የሰላም ድርድሩን በትክክለኛው መንገድ ለማስቀጠል እየጣሩ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።

እንደ ኢራን የዜና ወኪል አይ ኤስ ኤን ኤ /ISNA/ ዘገባ፣ አባስ አራግቺ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን “ጦርነቱን ሙሉ በሙሉ በማስቆም ላይ ኢራን ያላትን አቋም እና አመለካከት” ለማንፀባረቅ ከፓኪስታን ባለስልጣናት ጋር ለንግግር ተቀምጠው ነበር።ሚኒስትሩ እስከ ትናንት ቅዳሜ ኢስላማባድ የነበሩ ሲሆን ከዚያም ወደ ኦማን ተጉዘዋል። ሌሎች የኢራን ልዑኮች ደግሞ “ጦርነቱን ከማስቆም ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ አስፈላጊውን መመሪያ ለማግኘት” ወደ ቴህራን ተመልሰው ነበር ሲል የዜና አውታሩ ገልጿል።

አባስ አራግቺ ቅዳሜ ምሽት የፓኪስታን መዲና እስላማባድን ለቀው በመውጣታቸው በሁለተኛው ዙር በሚደረገው ውይይት ዙሪያ ግራ መጋባት ፈጥሮ ነበር። ነገር ግን ወደ ሞስኮ ከማምራታቸው በፊት ዛሬ ወደ ኢስላማባድ ተመልሰዋል ሲሉ የኢራን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ዋይት ሀውስ ዓርብ ዕለት ለሁለተኛ ዙር ውይይት ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነርን ያካተተ የልዑካን ቡድን ወደ ኢስላማባድ እንደሚልክ አስታውቋል። ነገር ግን የአራግቺ ፓኪስታንን ለቀው መውጣታቸው ከተዘገበ ብዙም ሳይቆይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ያለው ውይይት መሻሻል አላሰየም በሚል ተልዕኮውን አቋርጠነዋል ብለዋል። ትራምፕ አያይዘውም “በፈለጉት ጊዜ ሊደውሉልን ይችላሉ” ሲሉ ገልፀዋል።

DW Amharic


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2