ሰዎችን መሸከምና ማገዝ – እስከመቼ !!! ???

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በቅርባችን የሚገኙ በማንኛውም ደረጃ የምናገናቸው ሰዎች አንድ ደካማ ጎን ስላገኘንባቸው ብቻ የምንለያቸው ቢሆን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ብቻችንን እንደምንቀር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በተያያዘ ሁኔታ በአጠገባችን የሚገኙ ወዳጆቻችንም ሆኑ የስራ ባልደረቦቻችን አንድ ድካም ወይም ችግር እንዳዩብን ቢለዩን ከተመሳሳይ ብቻ የመቅረት ችግር አናመልጥም፡፡

ከሰዎች ጋር ጥቂት ካሳለፍን በኋላ እኛም የእነሱን አንዳንድ ደካማ ጎናቸውን ማየት፣ እነሱም የእኛ ደካማ ጎን ማየት መጀመራችን አይቀርም፡፡ ይህንን በፍጹም ልናስቀረው የማንችለው ማሕበራዊ ሂደት አልፈን ወደተረጋጋ ማሕበራዊ ግንኙነት ለመዝቅ ከፈለግን ሰዎችን ከድካማቸው ለይቶ በመመልከት ማስተናገድ የግድ ነው፡፡ ማለትም ድካማቸውንና ማንነታቸውን በማወቃችን ምክንያት ሳንንቃቸውና ሳናቃልላቸው ከሰዎቹ ጋር አብሮነትን የማዳበር ሰፊነት ማለት ነው፡፡

ይህ አመለካከትና የሕይወት ዘይቤ በቶሎ ልናስተናግደው የማንችለው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ ከአንዳንድ ሰዎቸ ጋር፣ እንኳን ደካማ ጎናቸውን ልንሸከም ቀርቶ ከእነሱ ጋር ለመገናኘት እንኳን ያለመፈለግ መብት እንዳለን ልናስብ እንችላለን፡፡ ይህ ደግሞ ልንሞግተው የማንችለው የግል አመለካከት ነው፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ የሕይወታችን ሂደቶች ውስጥ የሰዎችን ደካማ ጎን ተሸክሞና አልፎ የመዝለቅ ሁኔታ የግድ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡

1. ለወዳጅነት ስትል

ሰዎችን ከደካማ ጎናቸው ባሻገር በማየት አብሮነትን የማቆየትን ሰፊነት ከምንለማመድበት ምክንያት አንዱ ወዳጅነትን ለመጠበቅ ስንል ነው፡፡ የቅርብ ወዳጆቻችን የቅርብ ወዳጅ የሚሆኑትም ሆነ በዚያ የሚቆዩት ብርቱ ስለሆኑ ወይም ደካማ ስለሆኑ ሳይሆን ወዳጆቻችን ስለሆኑ ነው – አለቀ! ስለዚህም ደካማ ጎናቸውን አልፈን ወዳጃቸው ካልሆንን፣ ቀድሞውኑ የወዳጅነት ትርጉሙ አልገባንም ማለት ነው፡፡

2. ለሰዎቹ እድገት ስትል

አንዳንድ ጊዜ የሰዎችን ደካማ ጎን እስከ ጥጉ በመሸከም አብረኖነትን የምንጠብቅበት ምክንያት ሰዎቹ ካሉበት ሁኔታ ወጥተው ወደተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ለመርዳት ነው፡፡ ለእኛም ቢሆን እኮ፣ ቤተሰቦቻችን፣ አማካሪዎቻችን፣ አስተማሪዎቻችን፣ አሰልጣኞቸችንና እኛን ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑት ወዳጆቸን ያደረጉልንና እያደረጉልን ያለው ይህ ነው፡፡

3. ለዓላማ ስትል

አንዳንድ ከሰዎች ጋር ለማከናወን የፈለግነው ወሳኝ ዓላማ በጋራ በምንይዝበት ጊዜ እነሱም የእኛን፣ እኛም የእነሱን ደካማ ጎን የማለፍን ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ አንዳንድ ከአንድ ዓላማ ጀርባ የተሰለፉ ሰዎች የሚበሳጩበትና የሚለያዩበት ነገር ሲታይ ያስቃል፡፡ ታግሰን ማለፍ የሚገቡንን “ደካማ” ጎኖች ማለፍ እያቃተን ታላላቅ ዓላማዎችን የምንሰዋባቸው ጊዜያት ቀላል አይደሉም፡፡

ማሳሰቢያ፡- ዓላማ ከሌለውና ራስን ለጉዳት ከሚያጋልጥ የሰዎችን ደካማ ጎን ካለገደብ የመሸከም ዝንባሌ በሚገባ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

Dr eyob


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2