የነዳጅ እጥረቱን ተከትሎ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ዕለታዊ ተጓዦች ቁጥር 75 ሺሕ ደረሰ

- Advertisement -
Sidebar AD

በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ተከትሎ፣ እለታዊ የቀለል ባቡር ትራንስፖርት የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ወደ 75 ሺሕ ማደጉን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አስታውቋል።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ብርሃን አበባው ለአሐዱ እንደገለጹት፣ የነዳጅ እጥረት ከመከሰቱ በፊት በቀን በአማካይ 45 ሺሕ ሰዎች በከተማ ቀላል ባቡር ይጓጓዙ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የተጓዦች ቁጥር በ30 ሺሕ ጭማሪ አሳይቷል።

ይህንን ከፍተኛ ፍላጎት ለማስተናገድም በጥገና ላይ ያሉ ባቡሮች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

ድርጅቱ የተጓዦችን መጨናነቅ ለመቀነስ በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓታት ሁለት ባቡሮችን በአንድ ላይ በማያያዝ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነም ተነግሯል።

በአሁኑ ወቅት በሁሉም መስመሮች አገልግሎት እየሰጡ ያሉት 17 ባቡሮች ብቻ መሆናቸውን ያስታወሱት ዶክተር ብርሃን፣ በሚቀጥለው አንድ ወር ቢያንስ ሁለት ተጨማሪ ባቡሮችን ወደ ሥራ ለማስገባት መታቀዱን ለአሐዱ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ለዓመታት የቆየ የበጀት እጥረት እንዳለበት የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ በዚህ ምክንያት ለጥገና የሚውሉ ተለዋጭ ዕቃዎችን መግዛት ባለመቻሉ 20 ባቡሮች ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ድርጅቱ በአጠቃላይ 41 ባቡሮች ቢኖሩትም፣ በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ያሉት ግማሽ ያህሉ ብቻ ናቸው ተብሏል። የበጀት ችግሩ ተፈትቶ ባቡሮቹ ወደ አገልግሎት ቢመለሱ አሁን ያለውን የትራንስፖርት መጨናነቅ በከፍተኛ ሁኔታ መፍታት እንደሚቻል ተመላክቷል።

የኃይል መቆራረጥ በሚያጋጥምበት ወቅት ፈጣን ጥገና ለማድረግ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር የጋራ ቡድን መዋቀሩንም ዶክተር ብርሃን ጠቁመዋል።

ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ጥገናቸው ተጠናቅቆ ከሚወጡት ሁለት ባቡሮች በተጨማሪ፣ አነስተኛ ብልሽት ያለባቸውን ባቡሮች አገልግሎት ከሚሰጡት ጋር በማያያዝ የትራንስፖርት አቅሙን ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ተብሏል።

በ ሙሉጌታ በላይ


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: