#FastMereja I ያለፈው ሚያዝያ 16 ቀን 2018 ዓ.ም በመርካቶ ቆርቆሮ ተራ አካባቢ ተከስቶ በነበረው ከባድ የእሳት አደጋ፣ የሚርገበገብ ጭስና ሊፈነዳ የሚችልን ሲሊንደር የገዛ ህይወቱን ሳይሰስት አቅፎ በመሸከም የሺዎችን ህይወት የታደገው ጀግናው የእሳት አደጋ ሰራተኛ (ፋየር ፋይተር)፣ በደረሰበት ጉዳት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ዛሬ በሙሉ ጤንነት ወደ ስራ ገበታው ተመልሷል።
በአደጋው ወቅት እጅግ አደገኛ የነበረውን ሁኔታ ተቋቁሞ፣ ሊፈነዳ የተቃረበን ሲሊንደር ተሸክሞ በመውጣት ጥልቅ የሆነ የሕዝብ ወገንተኝነትና መሰዋዕትነት ያሳየው ይህ ጀግና፤ በተቋሙ ታሪክ የማይዘነጋ ደማቅ አሻራ አስቀምጧል። ጀግናው በተከሰተው አደጋ ሳቢያ የተመረዘ አየር በመተንፈሱ ምክንያት በሆስፒታል በፅኑ ክትትል ሲደረግለት የቆየ ሲሆን፣ በህክምና ባለሙያዎች ከፍተኛ ጥረት አገግሞ ዛሬ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ተቀላቅሏል።
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከፍተኛ አመራሮች እና የሙያ ባልደረቦቹ ጀግናውን በታላቅ ደስታ የተቀበሉት ሲሆን፣ “የእሱ መመለስ ለሁላችንም ትልቅ ብርታትና የሞራል ስንቅ ነው” ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል። ይህ ግለሰብ ለሕዝብ አገልግሎት መቆም ምን ማለት እንደሆነ በተግባር ያሳየ የኮሚሽኑ ኩራት መሆኑም ተመልክቷል።
Source: FastMereja









No comments yet.