በአርባ ምንጭ በወጣት ላይ አሰቃቂ ግድያ የፈጸመው ግለሰብ በዕድሜ ልክ እስራት ተቀጣ

- Advertisement -
Sidebar AD

#FastMereja I በአርባ ምንጭ ከተማ ወጣት ነህምያ ተስፋዬን በስለት ወግቶ በመግደልና በከባድ ውንብድና ወንጀል የተከሰሰው ማሙሽ ማርቆስ፣ በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት። ግለሰቡ ድርጊቱን የፈጸመው የካቲት 22 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት ላይ በሼቻ ክፍለ ከተማ በሚገኝ የአንድ ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ መሆኑ ተረጋግጧል።

እንደ ዐቃቤ ህግ ክስ እና ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ማስረጃ፣ ተከሳሹ ሟች ስልክ እያወራች ባለችበት ወቅት የዋጋ ግምቱ 17,000 ብር የሚያወጣ “Infinix” ስልክ ለመንጠቅ ሞክሯል። ወጣቷ ንብረቷን ለማስጠበቅ ባደረገችው ተቃውሞ ሳቢያ፣ ተከሳሹ በያዘው ስለታማ ቢላዋ ደረቷንና እጆቿን ደጋግሞ በመውጋት ከባድ ጉዳት አድርሶባታል። ወጣት ነህምያ ወደ ሆስፒታል ተወስዳ በሕክምና ሲረዳት ብትቆይም፣ በደረሰባት ከፍተኛ የደም መፍሰስ ምክንያት በዚያው ዕለት ሕይወቷ ሊያልፍ ችሏል።

ተከሳሹ ማሙሽ ማርቆስ በመጀመሪያ መከላከያ እንደሚያቀርብ ቢገልጽም፣ በሂደቱ ግን “የማቀርበው መከላከያ የለኝም፤ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እቀበላለሁ” በማለት ቃሉን ሰጥቷል። የአርባ ምንጭ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዐቃቤ ሕግን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች መርምሮ፣ ተከሳሹ በ1997 የወጣውን የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 671 (2) በመተላለፍ ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቶታል።

ፍርድ ቤቱ የጥፋተኛውን ድርጊት አሰቃቂነትና የወንጀሉን ክብደት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ግለሰቡ ቀሪ ዘመኑን በወህኒ እንዲያሳልፍ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ውሳኔ አስተላልፏል።


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2